"ለውጭ ዜጎችና ለስደተኞች በራችሁን አትዝጉ" - ፖፕ ፍራንሲስ
የሮማው ሊቀ ጳጳስ በአውሮፓ እየጨመረ ስለመጣው ብሔርተኝነትና አደጋው በሀንጋሪ መልዕክት አስተላልፈዋል
የአባ ፍራንሲስ መልዕክት ከጠቅላይ ሚንስትር ቪክተር ኦርባን ጸረ-ስደተኛ ፖሊሲዎች ተቃራኒ ነው ተብሏል
የሮማው ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ሀንጋሪውያን በስደተኞች እና በውጭ ሀገር ዜጎች ወይም "ከእኛ በተለዩ" በሚሏቸው ሰዎች ላይ በራቸውን እንዳይዘጉ አሳስበዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በሀንጋሪ ቡዳፔስት አደባባይ ያደረጉትን ንግግር ከ50 ሽህ በላይ ሰዎች መታደማቸው ተነግሯል።
አባ ፍራንሲስ በአውሮፓ ብሔርተኝነት እየጨመረ መምጣቱንና አደጋውንም አንስተዋል።
መልዕክታቸውን በወንጌል አውድ ያስቀመጡት የሮማው ሊቀ ጳጳስ፤ ለደስደተኞች በሮችን መዝጋት ከኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ ጋር የሚቃረኑ ናቸው ብለዋል።
የአባ ፍራንሲስ መልዕክት ከጠቅላይ ሚንስትር ቪክተር ኦርባን ጸረ-ስደተኛ ፖሊሲዎች ተቃራኒ ነው ተብሏል።
ጠቅላይ ሚንስትር ኦርባን ሀንጋሪ ወደ "ስደተኛ ሀገር" እንድትለወጥ እንደማይፈቅዱ ተናግረዋል።
ለዚህም ምክንያት ሲጠቅሱ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የስደተኛ ሀገር በመሆን በአገሬው ተወላጆች ዘንድ የማይታወቁ ሆነዋል የሚል ነው።
የ86 ዓመቱ አባ ፍራንሲስ በስብከታቸው ላይ ሀንጋሪዎች ኢየሱስን ለመከተል ከፈለጉ "የተዘጋውን የግላዊነት በሮች ለችግረኞች እና ለተሰቃዩ ሰዎች መክፈት አለባቸው" ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ድህነትን የሚሸሹ ስደተኞች አቀባበል እና ውህደት ሊደረግላቸው ይገባል ብለው እንደሚያምኑ መናገራቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።