ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ “ዓለም ለሰላም እየተራበች ነው” አሉ
አባ ፍራንሲስ ትርጉም የለሽ ጦርነት በአስቸኳይ እንዲያስቆም ስልጣን ያላቸውን ሰዎች አእምሮ ያብራልንም ብለዋል
አባ ፍራንሲስ በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል ውይይት እንደገና እንዲጀመር ጠይቀዋል
የሮማው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ በገና በዓል መልዕክታቸው በዩክሬን ያለው ጦርነት እና ሌሎች ግጭቶች እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
አባ ፍራንሲስ ቡራኬ እና መልእክት ሲያደርሱ ዓለም “በሰላም ረሃብ” እየተሰቃየች ነው ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ሆነው በተመረጡበት ስስፍራ “በዓለም ላይ ባሉ ቦታዎች ሁሉ ሰላም የሚናፍቁትን የህጻናት ሁሉ ፊት እንይ" ብለዋል።
በአስር ወራትን በደፈነው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ባደረሰው ውድመት ከቤታቸው ርቀው በጨለማ እና በቅዝቃዜ የገና በዓል ላይ የሚገኙትን የዩክሬን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ፊት እንይ ብለዋል።
“የሚሰቃዩትን ሁሉ ለመርዳት ተጨባጭ የአብሮነት ምልክቶችን እንድናቀርብ ጌታ ያነሳሳን።
የጦር መሳሪያ ነጎድጓድን ለማፈን እና ትርጉም የለሽ ጦርነት በአስቸኳይ እንዲያስቆም ስልጣን ያላቸውን ሰዎች አእምሮ ያብራልን" ሲሉ አባ ፍራንሲስ ተናግረዋል።
የዩክሬን ግጭት፣ በሌሎች ግጭቶች ወይም ሰብዓዊ ቀውሶች ሕይወታቸው ለተመሰቃቀለ ሶሪያ፣ ምያንማር፣ ኢራን፣ ሄይቲ እና የአፍሪካ የሳህል ክልል ያሉ ሰዎች አሳቢነት መቀነስ የለበትም ብለዋል።
"ጊዜያችን ከፍተኛ የሆነ የሰላም ረሃብ እየገጠመን ነው" ብለዋል።
አባ ፍራንሲስ ኢየሱስ በተወለደበት በቅድስት ሀገር በእስራኤል እና በፍልስጤማውያን መካከል ውይይት እንደገና እንዲጀመር ጠይቀዋል።
ረሀብ ለጦር መሣሪያ መዋሉንም ኮንነዋል። በዩክሬን ያለው ጦርነት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን አፍጋኒስታን እና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ጠቅሰው ምግብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀምን አውግዘዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።