“ደም መፋሰስን ተላምደን ማደግ አንችልም” - የሮማው ጳጳስ አባ ፍራንሲስ
ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ 45 ሚሊዮን የሚጠጉ የካቶሊክ አማኞች መኖሪያ ሀገር ናት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኮንጎ ጉዳይ ችላ ማለቱን አውግዘዋል
ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ በሀገሪቱ የሚሰተዋሉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ሊቆሙ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አባ ፍራንሲስ ይህን ያሉት ከፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በነበራቸው ውይይት ነው፡፡
ወይይቱ በምስራቅ ኮንጎ ያለው ቀጣይ ግጭት እና የኢኮኖሚ ቅኝ ግዛትን ጨምሮ በሀገሪቱ ላይ ተጽዕኖ በሚፈጥሩ በጣም ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጉብኝት በሰሜን ኪቩ ግዛት በኤም-23 አማጺያን እና በመንግስት ወታደሮች መካከል በአንጎላ የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ባሉበት ወቅት መሆኑ ነው፡
እናም የአባ ፍራንሲስ የኮንጎ ጉብኝት የበርካታ ለአስርት አመታት ያህል የንጹሃን ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ የሚገኘው የኮንጎ ግጭት ዓለም ችላ እንዳይለው ለማሳሰብ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
አባ ፍራንሲስ ከፖለቲከኞች እና ከተለያዩ አካላት ጋር በነበራቸው ቆይታ ባደረጉት ንግግር “ለአስርት አመታት የዘለቀውን ደም መፋሰስ ተላምደን መኖር አንችልም ፡፡ እኔ በጣም የማበረታታቸው አሁን ያሉት የሰላም ሂደቶች በተጨባጭ ተግባራት ሊቀጥሉ ይገባል፣ ቃል ኪዳኖችም ሊጠበቁ ይገባል” ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፤ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኮንጎ ጉዳይ ችላ ማለቱም አውግዘዋል።
ኮንጎዎች ሁከትን ሊቃወሙ ይገባል ያሉት አባ ፍራንሲስ፤ ልማትንና ሰላምን ለመደገፍ አዲስ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።
"ከአናንተ ጋር ቆሜያለሁ እናም ለዚች ታላቅ ሀገር የወደፊት ሰላም፣ ስምምነት እና ብልጽና እጸልያለሁ፡፡ እግዚአብሔር መላውን የኮንጐ ህዝብ ይባርክ” ሲሉም ነው የተደመጡት አባ ፍራንሲስ በፕሬዝዳንት ቤተ መንግስት ለተገኙት ታዳሚዎች ባደረጉትና በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች በአደባባይ ስክሪኖች በተከታተሉት ንግግራቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ በበኩላቸው አሁን ባለው ችግር ውስጥ “የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝምታ ምምረጡ” አሳዝኖኛል ሲሉ ተናግረዋል።
ኮንጎ በመጪው ታህሳስ ወር የምታካሂደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ግልጽ እና ተዓማኒ እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡
ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ 45 ሚሊዮን የሚጠጉ የካቶሊክ አማኞች መኖሪያ ሀገር ናት፡፡
የአሁኑ የአባ ፍራንሲስ ጉብኝት ኮንጎ ከ38 ዓመታት በፊት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን ከተቀበለች ወዲህ የተደገረ የመጀመሪያውና ታሪካዊ ጉብኝት መሆኑ ነው፡፡