የሮማው ጳጳስ አባ ፍራንሲስ በ2013 የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው እንደነበር ገለጹ
አባ ፍራንሲስ አሁን ላይ ጥሩ በሚባል ጤንነት ሁኔታ ላይ ነኝ ብለዋል
ፍራንሲስ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን አባላት ያላትን የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስትያንን እንደሚመሩ ይታወቃል
የሮማው ጳጳስ አባ ፍራንሲስ እንደፈረንጆቹ በ2013 ከተመረጡ በኋላ አንድ ቀን አስቸጋሪና ከአቅም በላይ የሆነ የጤና እክል ቢገጥመኝ በሚል የመልቀቂያ ደብዳቤ እስከማስገባት ደርሰው እንደነበር ገለጹ፡፡
ቅዳሜ እለት ድፍን 86 አመት የሆናቸው አባ ፍራንሲስ አሁን ላይ ከሚሰማቸው የጉልበት ህመም በስተቀር በጥሩ ጤንነት ላይ መሆናቸውም አስታውቀዋል፡፡
አባ ፍራንሲስ ደብዳቤውን የሰጡት በወቅቱ ጳጳሳት ለነበሩት የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብጹዕ ካርዲናል ታርቺስዮ በርቶነን እንደነበርም ከስፔኑ ኤቢሲ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል፡፡
"የስልጣን መልቀቂያዬን አስቀድሜ ፈርሜያለሁ። ታርቺስዮ በርቶነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበር:: መልቀቂያ ፈርሜያለሁ አልኩት፤ የደብዳቤው ይዘት በህክምና ምክንያት ወይም በማንኛውም ነገር እንቅፋት ቢፈጠር ስራዬን መልቀቄ ነው ” የሚል እንደነበርም ነው አባ ፍራንሲስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ የገለጹት፡፡
ፍራንሲስ 1ነጥብ 3 ቢሊየን አባላት ያላትን የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስትያንን ከመምራት ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ካጋጠማቸው ስልጣን እንደሚለቁ ብዙ ጊዜ ሲናገሩ መቆየታቸው አይዘነጋም።