ምርጫ ቦርድ የኦነግን ጠቅላላ ጉባኤ እና ጉባኤው ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲቀበል ፍርድ ቤቱ ወሰነ
“ጠባብ ቢሆንም በምርጫው የመሳተፍ ዕድል አለን”- ቄጀላ መርዳሳ
ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤውንና በጉባኤው የተላለፈውን ውሳኔ እንደማይቀበል ማስታወቁ የሚታወስ ነው
የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ያደረገውን የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ እና በስብሰባው ያሳለፈውን ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲቀበለው ወሰነ፡፡
የኦነግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት በቦርዱ እና በፓርቲያቸው መካከል የነበረው ክርክር ዛሬ እልባት አግኝቷል፡፡
ኦነግ በውስጥ ችግሩ ምክንያት ጠቅላላ ጉባዔ ሳያካሂድ በመቆየቱ “የምርጫና የዕጩ ምዝገባ ጊዜ አልፎብናል” በማለት ቦርዱ ችግሩን ግምት ውስጥ በማስገባት የምልክት መረጣና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዲያደርግ እንዲፈቅድለትና ጠቅላላ ጉባኤውንም እንዲያጸድቅለት ቦርዱን በደብዳቤ ጠይቆ ነበር።
ቦርዱም የቀረቡትን ሰነዶች በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት መርምሮ ባሳለፈው ውሳኔ፤ አዲስ የተመረጡትን የኦነግ አመራሮች እና የተካሔደውን ጉባኤ እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡
ውሳኔውን በማስመልከት መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “የተከናወነው ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት የለውም”በማለት ወስኖ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ኦነግ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ያደረገው ጠቅላላ ጉባኤና ያሳለፈው ውሳኔ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይግባኝ ብሎ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ሆኖም ቦርዱ ይግባኙን አለመቀበሉን ተከትሎ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ተወስዶ ነበር፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ይግባኝ ባይ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ያደረገው ጠቅላላ ጉባኤና ያሳለፈው ውሳኔ ተቀባይነት አለው ብሏል፡፡
ቦርዱ ኦነግ ያደረገውን ጠቅላላ ጉባዔ እና የተወሰነውን ውሳኔ እንዲያስፈጽምም ፍርድ ቤቱ የወሰነው፤ እንደ ምክትል ሊቀመንበሩ ቀጄላ መርዳሳ ገለጻ፡፡
በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ኦነግ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ አዲስ የአመራር አባላትን መምረጡ ይታወሳል፡፡
በምርጫው መሰረትም አቶ አራርሶ ቢቂላ ሊቀመንበር፣ አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና አቶ ብርሃኑ ለማ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን አል ዐይን አማርኛ በወቅቱ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
አቶ ቀጄላ “ውሳኔው በምርጫ እንድትወዳደሩ ያደርጋችኋል ወይ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ጠባብ ቢሆንም በምርጫው ለመሳተፍ የሚያስችል የተወሰነ ዕድል አለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አል ዐይን ውሳኔውን በማስመልከት የቦርዱን ምላሽ ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡