በኮንጎ ያለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር 20 ሰላማዊ ሰዎችን ተኩሶ በመግደል ተከሷል
ዲሞክራቲክ ኮንጎ በሀገሯ ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ሰላም አስከባሪ ጦር ቃል አቀባይን አባረረች።
በዲሞክራቲክ ኮንጎ የአማጺያንን ጥቃት ለመመከት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላም አስከባሪ ማሰማራቱ ይታወሳል።
ይሁንና በዲሞክራቲክ ኮንጎ የተለያዩ ስፍራዎች የተሰማራው ይህ ሰላም አስከባሪ ጦር ንጹሀን ዜጎችን ከአማጺያን ጥቃት ሊያስጥለን አልቻለም በሚል ይተቻል።
የዲሞክራቲክ ኮንጎ ዜጎችም ባሳለፍነው ሳምንት የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦርን ተቃውመው ሰልፍ አካሂደዋል።
ዜጎቹ በሀገራቸው የተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር የዲሞክራቲክ ኮንጎ ዜጎችን ከታጣቂዎች ጥቃት አልታደገም በሚል ከረር ያለ ተቃውሞ አሰምተው ነበር።
በዚህ ታቃውሞ ደስተኛ ያልሆነው በስፍራው ያለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ዜጎች ጥይት ተኩሶ ተቃዋሚ ዜጎች ላይ ጉዳት አድርሷል።
በዚህ ተኩስ ምክንያት 36 ሰዎች ሲገደሉ ከ15 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ይህንን የዜጎች መሞት ተከትሎ የዲሞክራቲክ ኮንጎ መንግስት እና በስፍራው ያለው የተመድ ሰላም ማስከበር ተልእኮ ጋር አለመግባባቶች ተከስተዋል።
በኬንሺያሳ የተመድ ተልዕኮ ቢሮ ቃል አቀባይ ማቲያስ ጊልማን ያልተገባ እና ግጭት አባባሽ መግለጫ ሰጥተዋል በሚል በዲሞክራቲክ መንግስት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ተወስኖባቸዋል።
በዲሞክራቲክ ኮንጎ ተመድ ላሰማራው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጦር ውስጥ ጦር ካዋጡ ሀገራት መካከል አንዷ ታንዛኒያ ነች።
የታንዛኒያ ጦርም ባሳለፍነው ሳምንት በተከሰተው ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥይት በመተኮስ እና በመግደል ክስ ቀርቦባቸዋል።
እነዚህ የሰላም አስከባሪ ጦር አባላትም ወደ ሰላማዊ ዜጎች ጥይት በመተኮስ እና በመግደል በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉ ይታወሳል።