በቤልጂየም የኮንጎ ቅኝ ግዛት ዘመን 10 ሚሊየን ዜጎች በረሃብ እና በበሽታዎች እንደሞቱ ጥናቶች ያለመክታሉ
ቤልጂየም በቅኝ ግዛት ዘመን በዲሞክራቲክ ኮንጎ በሰራችው ጥፋት መጸጸቷን ገለጸች።
ቤልጂየም ከፈረንጆቹ 1885 እስከ 1960 ባሉት 75 ዓመታት ውስጥ ዲሞክራቲክ ኮንጎን ቅኝ ግዛት የገዛች ሲሆን፤ በነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ በደሎችን እንደፈጸመች አምናለች።
በአጠቃላይ በቤልጂየም የኮንጎ ቅኝ ግዛት ዘመን 10 ሚሊየን ዜጎች በረሃብ እና በበሽታዎች እንደሞቱ ሮይተርስ የተለያዩ ጥናቶችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ንጉስ ፊሊፕ የቀድሞ ቅኝ ግዛት የነበረችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ኮንጎን ከጎበኙ በኋላ ለሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት ፊት ንግግር አድርገዋል።
ንጉስ ፊሊፕ እንዳሉት ሀገራቸው በቅኝ ግዛት ዘመን ለተፈጸሙ በደሎች መጸጸታቸውን ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
ንጉሱ አክለውም ቤልጂየም በዲሞክራቲክ ኮንጎ ምድር ዘረኛ እና ገና ያልተገለጠ በደል መፈጸሟን በጸጸት ተናግረው፤ ሀገራቸው በቅኝ ግዛት ዘመን ያደረሰችው ጉዳት አሁን ያለውን ትውልድ በመጉዳት ላይ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ይሁንና በርካታ የኮንጎ ፖለቲከኞች ቤልጂየም በቅኝ ግዛት ዘመን የፈጸመችውን በደል አምና ባቀረበቸው የይቅርታ መልዕክት ቢደሰቱም ይህ ግን ብቻውን በቂ አይደለም በማለት ላይ ናቸው።
የኮንጎ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆኑት ሙዩምባ ንካንጋ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ከቤልጂየም ይቅርታን እና ጸጸትን እንጠብቅ ነበር ነገር ግን ግፍ የደረሰባቸው የኮንጎ ዜጎች ከዛ ያለፈ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።
ቤልጂየም በቃላት ሊነገሩ የማይችሉ በደሎችን በኮንጎ ዜጎች ላይ ፈጽሟል ጉዳዩ በይቅርታ እና በጸጸት ብቻ የሚታለፍ አይደለም የሚሉት እኝህ ፖለቲከኛ ምርመራ ተደርጎ ፍትሀዊ ውሳኔ በደሎችን ሊያስረሳ የሚችሉ ስራዎችን አሁን ካለው የቤልጂየም መንግስት እንጠብቃለን ሲሉም አክለዋል።