ድርቅ በኢትዮጵያ 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎችን ችግር ላይ ጥሏል ተባለ
ሱማሌ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች በድርቅ የተጎዱ የሃገሪቱ አካባቢዎች ናቸው
ዜጎቹ አስቸኳይ የምግብ እርዳታን እንደሚፈልጉ ተገልጿል
ድርቅ በኢትዮጵያ ከ6 ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎችን ችግር ላይ ጥሏል ተባለ፡፡
ዜጎቹ በድርቁ ክፉኛ ተጎድተዋል ያለው የተመድ ሰብዓዊ መብት ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አስቸኳይ የምግብ እርዳታን እንደሚፈልጉ ገልጿል፡፡
በፓሲፊክ ውቂያኖስ ላይ ያለው የሙቀት መጠን መቀነሱን ተከትሎ ያጋጠመ ነው የተባለለት ድርቁ ሶስት የሃገሪቱን ክልሎች ማለትም ሶማሊያን፣ ኦሮሚያን እና ደቡብ ክልልን አጥቅቷል፡፡
በድርቁ የተጎዱ ዜጎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን በመጨመርም ላይ ይገኛል እንደ ኦቻ ገለጻ፡፡ ኦቻ ባወጣው ሪፖርት መሰረት በኢትዮጵያ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡
በሱማሌ ክልል ሶስት ሚሊዮን ፣በምስራቅ ኦሮሚያ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን እንዲሁም በደቡብ ክልል 1 ሚሊዮን ዜጎች በድርቁ ክፉኛ ተጎድተው የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ችግሩ ከአሁን ቀደምም የነበረ መሆኑ አርሶ እና አርብቶ አደሮቹ አሁን የተፈጠረባቸውን የድርቅ ጉዳት መቋቋም እንዳይችሉ ማድረጉን የድርጅቱ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ድርቁ በተለይም በሱማሌ ስድስት ዞኖች፣ በምስራቅ ኦሮሚያ ጉጂ እና ቦረና ዞኖች ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችልም ድርጅቱ አስጠንቅቋል፡፡
በነዚህ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ አርብቶ አደሮች እንስሳቶቻቸውን ከሞት ለማዳን እስከ 300 ኪሎ ሜትር ድረስ እየተሰደዱ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ድርቁ በተለይም ህጻናት፣ነፍሰ ጡር እናቶች እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን የበለጠ በመጉዳት ላይ ነው ያለው ድርጅቱ ለተጎጂዎች በአፋጣኝ ድጋፍ ያስፈልጋልም ብሏል፡፡
በምስራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ቁጥር እንዳሻቀበውም ነው የተገለጸው፡፡
በተያያዘ ዜና የበረሃ አንበጣ ከአፍሪካ ቀንድ ሙሉ ለሙሉ መጥፋቱን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ፋኦ ገልጿል፡፡
ፋኦ ላለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን ጨምሮ በኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ እና ጅቡቲ በበረሃ አንበጣ ሲጠቁ ቆይተዋል፡፡
ይሁንና በአፍሪካ ቀንድ አገራት በየካቲት ወር በተደረገ ቅኝት ለመጀመሪያ ጊዜ የበረሃ አንበጣ መኖሩን የሚያረጋግጥ መረጃ አለመገኘቱን ድርጅቱ ገልጿል፡፡