በኢትዮጵያ ድርቅ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ከሚያዚያ በፊት ዝናብ አያገኙም ተባለ
ድርቁ የተከሰተው በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ የሙቀት መጠኑ በመቀነሱ ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሶስት ክልሎች ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል አስቀድሞ ለፌደራል እና ክልል ተቋማት ማድረሱን ገልጿል
በኢትዮጵያ ድርቅ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ከሚያዚያ በፊት ዝናብ እንደማያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ በሶማሊ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች ከፍተኛ የውሃ እጥረት ያጋጠማቸው ሲሆን እጥረቱ ከክልሎቹ አቅም በላይ በመሆኑ ድርቁ በሰው እና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት መሞታቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባሳለፍነው ሳምንት ማሳወቁ ይታወሳል።
በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ መነሻው ባሳለፍነው ክረምት ወራት ውስጥ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ በመዝነቡ እና በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ ምንም ዝናብ አለመዝነቡ ቢሆንም፤ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ባሉት ወራት ውስጥ ዝናቡ አለመዝነቡ ጉዳቱን አባብሶታልም ተብሏል።
በኬንያ ብቻ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን እንስሳት በድርቁ ምክንያት የሞቱ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ 240 ሺህ የቤት እንስሳት መሞታቸውን ፋኦ በሪፖርቱ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትት የአየር ሁኔታ እና ትንበያ ባለሙያው አቶ ታምሩ ለአል ዐይን አማርኛ እንገለጹት አሁን ላይ ድርቅ የተከሰተባቸው አካባዎች ከሚያዝያ በፊት ዝናብ እንደማያገኙ ተናግረዋል፡፡
ድርቁ በሶማሊ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች መከሰቱን የተናገሩት አቶ ታምሩ ወደ ኢትዮጵያ ሞቃታማ አየር በመንፈስ ለዝናብ መከሰት ምክንያት ከሆነው አንዱ የሆነው የፓሲፊክ ውቂያኖስ ዝቅተኛ ሙቀት መመዝገቡ ለድርቁ መከሰት ዋነኛው ምክንያት መሆኑንም አክለዋል፡፡
በዚህ ውቂያኖስ ላይ ያለው ቅዝቃዜ ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ እየተሸሻለ ስለሚመጣ ከሚያዝያ ጀምሮ አካባቢዎቹ መደበኛ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉም አቶ ታምሩ ጠቅሰዋል፡፡
ድርቅ በተከሰተባቸው በነዚህ ክልሎች የዝናብ እጥረት ሊከሰት እንደሚችል በቅድመ የአየር ንብረት ትንበያ ሪፖርታችን ለፌደራል እና ክልል ተቋማት አስቀድመው ዝግጅት እንዲያደርጉ ማሳወቃቸውን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
ከነዚህ በተጨማሪ ግን ደቡብ ትግራይ፣ምስራቅ አማራ፣ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ የባሌ አካባቢዎች፣ አፋር ክልል፣ ሰሜን ሶማሊ፣ሁለቱ የሀረርጌ ዞኖች እንዲሁም የምእራብ ኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች ከያዝነው የካቲት ወር አጋማሽ ጀምሮ እስከ ግንቦት ወር ድረስ መደበኛ እና ከዚያ በላይ የበልግ ዝናብ እንደሚያገኙም የኢንስቲትዩቱ ቅድመ የአየር ጸባይ ትንበያ ሪፖርት ያስረዳል፡፡