በምስራቅ አፍሪካ ከ10 ሚሊየን በላይ ሰዎች በድርቅ ምክንያት ለረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን ተመድ ገለጸ
በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በርካቶች በድርቅ ሳቢያ መጎዳታቸው ተገልጿል
በሀገራቱ ለተከሰተው ድርቅ ምለሽ የሚሆን 327 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልገውም ተመድ አስታውቋል
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በምስራቅ አፍሪካ ሀገራተት በቀጠለው ድርቅ ሳቢያ በርካቶች ለረሃብ እየተጋለጡ ነው ብሏል።
እንደ ድርጅቱ ገለፃ በሀገራቱ 13 ሚሊየን ሰዎች ለከፋ ረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል።
የግብርና ስራዎችን አለመስራት እንዲሁም የምግብ እጥረት በርካቶች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል ያለው ድርጅቱ፤ በቀጠናው ሊደረስ የሚችለውም የሰብአዊ ቀውስ ለመግታት አስቸኳይ ድጋፎችን ያስፈልጋሉ ብሏል።
በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ ሳቢያ ድርቁ መቀጠሉንም ነው ድርጅቱ ያስታወቀው።
በዚህም የእርሻ ስራ መቆሙን እና የቀንድ ከብቶች እየሞቱ ነው ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፤ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የሚገኙ 13 ሚሊየን ሰዎች ለረሃብ ሊጋለጡ ተቃርበዋልም ብሏል።
በእነዚህ ሀገራት በአስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፎች ካልተደረጉ የሚደርሰው ሰብአዊ ድጋፍን ማስቆም አዳጋች እንደሚሆንም አሳስቧል።
በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለተከሰተው ድርቅ ምለሽ የሚሆን 327 ሚሊየን ገንዘብ እንደሚያስፈልገውም ነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያስታወቀው።
ገንዘቡም በአጭር ጊዜ ምግብ እና ጥሬ ገንዘብ ለተጎጂዎች ለማቅረብ እንዲሁም በረጅም ጊዜ ደግሞ ከአየር ፀባይ ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ለድርቅ የተጋለጡ አካባቢዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚውል ነው ብሏል።