ዱባይ የአለማችን ሁለተኛውን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ እየገነባች ነው
ከቡርጀ ከሊፋ በቅርብ ርቀት እየተገነባ የሚገኘው “ቡርጀ አዚዚ” 725 ሜትር ቁመት ይኖረዋል ተብሏል
131 ፎቆች የሚኖሩት ረጅም ህንጻ ባለሰባት ኮከብ ሆቴሎችና አፓርትመንቶችን ማካተቱ ተገልጿል
የአለማችን ቁጥር አንድ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ መገኛዋ ዱባይ ሁለተኛውን ረጅም ህንጻ እየገነባች ነው ተባለ።
“ቡርጀ አዚዚ” 828 ሜትር ቁመት ያለውን “ቡርጀ ከሊፋ” ተከትሎ ሁለተኛው ሰማይ ጠቀስ ህንጻ እንደሚሆን በትናንትናው እለት ነው የተገለጸው።
በ2024 ጥር ወር ቁፋሮው የተጀመረው “ቡርጅ አዚዚ” ከኤምሬትስ የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን እና ከሌሎች ተቋማት የሚሰጠው የግንባታ ፈቃድ ሲጠበቅ ቆይቷል።
በዚህም ምን ያህል ፎቆች ያሉት ህንጻ እንደሚገነባ ሳይነገር ቆይቷል ።
የአዚዚ ዴቨሎፕመንትስ መስራች ሚርዋይስ አዚዚ በትናንትናው እለት ግን ሲጠበቅ የነበረውን መረጃ አጋርተዋል። “ያቀረብነው ሁለት ዲዛይኖችን ነው ባለ526 እና 725 ሜትር ቁመት ህንጻ፤ ባለ725 ሜትሩ ህንጻ ዲዛይን ጸድቆልናል” ሲሉ ለዘናሽናል ኒውስ ተናግረዋል።
ለሁለተኛውና ረጅሙ ህንጻ ዲዛይን ተጨማሪ የመሰረትና ቋሚ ግንባታዎችን ለማካሄድ አስቀድመን ተዘጋጅተናልም ነው ያሉት።
ከቡርጀ ከሊፋ በ103 ሜትር የሚያጥረው ሰማይ ጠቀስ ህንጻ 131 ፎቆች ይኖሩታል ተብሏል።
ረጅሙ ህንጻ ባለሰባት ኮከብ ቅንጡ ሆቴሎች እና ዘመናዊ አፓርትመንቶችን እንደሚያካትትም ነው አዚዚ ዴቨሎፕመንትስ ያስታወቀው።
ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደሚደረግበት የተነገረለት “ቡርጀ አዚዚ” በ2028 ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን በቀጣዩ አመት አፓርትመንቶችን መሸጥ ይጀምራል።
ከቡርጀ ከሊፋ በ3 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ረጅሙ ህንጻ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛው ሰማይ ጠቀስ ህንጻ የሆነውን የማሌዥያውን “ሜርደካ 118” (678 ሜትር) በመብለጥ ደረጃውን ይረከባል።
“ቡርጀ አዚዚ” ግንባታው ሲጠናቀቅ በርካታ የአለም ክብረወሰኖችን እንደሚይዝ ይጠበቃል፤ በሰፊ ሆቴልና ሬስቶራንት፣ ከፍታ ላይ በሚገኝ የመኝታ ክፍል (118ኛ ፎቅ) እና በሌሎች ቀደም ሲል የተያዙ ክብረወሰኖችን ይሰብራል ተሎ እንደሚጠበቅ አልሚው ኩባንያ አስታውቋል።