የሮቦቶቹ ተገጣጣሚ ክፍሎች ከሩስያ የሚመጡ ስለመሆናቸው ተነግሯል
አረብ ኢምሬትስ ዱባይ የአለማችን የመጀመሪያውን ሰው አልባ የሮቦት ካፌ ልትከፍት መሆኑ ተነግሯል።
ሮቦቶች የሚያስተናግዱባቸው ምግብ ቤቶችን በተለያዩ የአለም ከተሞች መመልከት እየተለመደ መጥቷል።
በዱባይ በ2023 ይከፈታል የተባለው “ዶና ሳይበር ካፌ” ግን ምንም አይነት የሰው ፍጡር አስተናጋጅ አይታይበትም ነው የተባለው።
መስተንግዶው ላይ ከላይ ታች የሚሉት ሮቦቶችም ደንበኞችን የሚስቡ ቆንጆዎች እንዲሆኑ ተደርጓል።“ሞዴል ሮቦቶቹ” እንኳን ከሩቅ ከቅርብም ለሚያያቸው ቆንጆ ሴት እንጂ የቴክኖሎጂ ውጤት አይመስሉም ተብሎላቸዋል።
የማይደክሙት ሮቦቶች 24 ስአት የሚሰሩ ሲሆን፥ ሲታዘዙ አይስክሬም በሚሰሩና ቡና በሚያፈሉ ማሽኖች ይታገዛሉ።
የሮቦቶቹ ተገጣጣሚ ክፍሎች ከሩስያ የሚመጡ ናቸው ተብሏል።
ሮቦ- ሲ2 የሚል ስያሜ የተሰጣት “ቆንጆ ሮቦት” አር ዲ አይ በተሰኘው የሮቦቲክስ ኩባንያ መሰራቱንም ነው ኢንዲያን ታይምስ ያስነበበው።
እንደ ሞዴል ሳቢ ሆነው የተሰሩት ሮቦቶች የሰው ልጆችን መልክ ብቻ ሳይሆን ባህሪ እንዲላበሱም ብዙ ተደክሞባቸዋል፤ ደንበኞችን የማስታወስ፣ አዳምጠው ምላሽ መስጠት፣ በተለያዩ ጉዳዮች የማውራት ችሎታ አላቸው።
ድብርት የተሰማው ደንበኛን ለማዝናናትም ልዩ ታሪክ ወይም ተረት መተረክና ጨዋታ መፍጠር እንዲችሉም ተደርጓል መባሉ ግርምትን ፈጥሯል።
በ2023 በዱባይ ይከፈታል የተባለው የዶና ሳይበር ካፌ በተለያዩ የኤምሬትስ ከተሞችም የማስፋፊያ ፕሮጀክት ስለመያዙም ነው የተነገረው።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ አስደናቂ ግስጋሴ ላይ የምትገኘው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአለም የመጀመሪያ የሚያደርጓትን ስራዎች እየከወነች ሲሆን፥ በቅርቡም በቆነጃጂት ሮቦቶች ብቻ የሚያስተናግድ ካፌ ይከፈትባታል።