ከኬንያ ወደ ዱባይ የሚደረጉ በረራዎች ታገዱ
ዱባይ እገዳውን የጣለችው በኬንያ የኦሚክሮን የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መዛመቱን ተከትሎ ነው ተብሏል

እገዳው በሁለቱ ሀገራት መካከል በሚደረጉ የካርጎ በረራዎች ተጽእኖ እንደሌለውም ነው የተገለጸው
የዱባይ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከኬንያ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እና ትራንዚት በረራዎችን በጊዜያዊነት ማገዱን አስታወቀ።
የእገዳው ምክንያት ግልጽ ባይሆንም፤ ዱባይ እገዳውን የጣለችው በኬንያ በከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ የሆነው የኦሚክሮን የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መዛመቱን ተከትሎ ሊሆን እንደሚችል ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
የዱባይ ባለስልጣናት “ከታህሳስ 20 ቀን 2021 ጀምሮ በኬንያ ሪፐብሊክ ውስጥ ከማንኛውም ቦታ ወደ ዱባይ ኤሚሬትስ የሚደረጉ በረራዎች ለ48 ሰአታት መቋረጡን ማሳወቅ እንወዳለን” ሲሉም አስታውቀዋል።
እገዳው በሁለቱ ሀገራት መካከል በሚደረጉ የካርጎ በረራዎች እንዲሁም ከዱባይ ወደ ናይሮቢ የሚጓዙ የመንገደኞች እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ አይኖረውም ነው የተባለው።
የዱባይ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ወደ ኬንያ የሚደረገው በረራ ዳግም ሲጀምር ተጓዦች የጉዞ ሰነዶቻቸውን እንዲይዙም ጠይቋል።
ዱባይ ከኬንያ በተጨማሪ በኮቪድ-19 ኮማንድ እና መቆጣጠሪያ ማእከል በኩል የኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ብሩንዲ፣ ናይጄሪያ፣ዛምቢያ፣ ካሜሩን እና ቻድ ተጓዦችን ስርጭት ለመግታት አዳዲስ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ ናት።