የዱባይ ኩባንያዎቹ ለኢትዮጵያ የቢዝነስ ቱሪዝም ወኪሎች ስልጠና ሰጡ
25 የዱባይ የቱሪዝም ኩባኒያዎች ዓለም አቀፍ ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት “የዱባይ ቱሪዝም መድረክ” በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው
ኢትዮጵያውያን ወደ ዱባይ በመሄድ ከአፍሪካ ሁለተኛ መሆናቸውን በዱባይ ቱሪዝም ዲፖርትመንት የሰብ ሰሃራ ኦፐሬሽን ዳይሬክተር ተናግረዋል
ኢትዮጵያውያን ያሏቸውን በርካታ መስህቦች ለዓለም ተደራሽ ቢያደረጉና የገበያ ትስስር ቢፈጥሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በዱባይ የቱሪዝም ዲፓርትመንት የሰብ-ሰሃራ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ስቴላ ፉባራ ተናገሩ፡፡
ዳይሬክተሯ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለውና በርካታ የሀገር ውስጥና የዱባይ ኩባኒያዎች እየተሳተፉበት ባለው የዱባይ ቱሪዝም መድረክ ላይ ነው፡፡
በመድረኩ መቀመጫቸው በዱባይ ያደረጉ 25 ኩባኒያዎች የወከሉ ዳይሬክተሮች የተገኙ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ልምድ አቅርበዋል፡፡
ኩባንያዎቹ በቱሪዝም፣ ሜዲካል ኢንዱስትሪ፣ አየር መንገድ፣ ሆቴል፣ እና በመዝናኛ መስክ የዳበረ ልምድ ያላቸው ናቸው ተብሏል፡፡
ኩባንያዎቹ በተለያዩ የቱሪዝም መስኮች ያላቸውን የዳበረ ልምድ በተመለከተ፤ 100 ለሚሆኑ የኢትዮጵያ የቢዝነስ ቱሪዝም ወኪሎች ስልጠና ሰጥተዋል፡፡
ስልጠናው በዘርፉ የተሰማሩ የኢትዮጵያ ኩባኒያዎች ዱባይ ከሚገኙ ኩባኒያዎች የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችላቸው ግንዛቤ እንዲጨነብጡ የሚያግዝ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በመድረኩ ንግግር ያሰሙት በዱባይ የቱሪዝም ዲፓርትመንት የሰብ-ሰሃራ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ስቴላ ፉባራ፤ የኢትዮጵያ ኩባኒያዎች ቅርብ ከሆነችው ዱባይ ጋር የቢዝነስ አጋርነት ቢፈጥሩ በየትኛውም መመዘኛ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ለአል-ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ዱባይ ከየትኛውም ሀገር በበለጠ ለኢትዮጵያ ቅርብ ናት ያሉት ዳይሬክተሯ፤ “ኢትዮጵያውያን ያሏቸውን በርካታ መስህቦች ለዓለም ተደራሽ ቢያደረጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ወደ ዱባይ በመጓዝ ሁለተኛ ደረጃ የሚይዙት ኢትዮጵያውያን መሆናቸው የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ “የሚያደርጉት ጉዞ ወደ ቢዝነስ ቢቀይሩት የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ”ም ብለዋል።
በኢትዮጵያ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ላይ ያሉት የዱባይ ኪባኒያዎች ዋና ትኩረት ያደረጉት ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ጋር የቢዝነስ ትስስር መፍጠር እንደሆነም በመድረኩ ተገልጿል፡፡
የኩባኒያዎቹ ዳይሬክተሮች አስካሁን በናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ መሰል የንግድ ልውውጥ መድረክ ያዘጋጁ ሲሆን፤ በቀጣይ ወደ ኡጋንዳ እና ኬንያ የሚሄዱ ይሆናል፡፡