በአፍጋኒስታን እና ፓኪስታን በደረሰ ርዕደ መሬት በጥቂቱ 13 ሰዎች ሞቱ
ንዝረቱ ከ1 ሺህ ኪሎሜትር በላይ የተሰማው ርዕደ መሬት እስካሁን በ90 ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱም ተገልጿል
በፓኪስታን በፈረንጆቹ 2005 በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 6 ሆኖ የተመዘገበ አደጋ የ73 ሺህ ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ ይታወሳል
በፓኪስታን እና አፍጋኒስታን የደረሰ ርዕደ መሬት በጥቂቱ የ13 ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ ተነግሯል።
በርዕደ መሬት መለኪያ (ሬክተር ስኬል) 6 ነጥብ 5 ሆኖ የተመዘገበው አደጋ ከ90 በላይ ሰዎች ላይም ጉዳት ማድረሱ መገለጹን ሬውተርስ ዘግቧል።
በፓኪስታን 9 ሰዎችን የቀጠፈው አደጋ 44 ሰዎችን ማቁሰሉን ያስታወቀው የሀገሪቱ መንግስት፥ በሰሜን ኪይበር ፓክቱንክዋ ግዛት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ገልጿል።
የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው በርካታ ቤቶችን ማፈራረሱም ነው የተገለጸው።
ንዝረቱ ከ1 ሺህ ኪሎሜትር በላይ ከፓኪስታን ጀምሮ ህንድ፣ ኡዝቤኪስታን፣ ታጂኪስታን፣ ካዛኪስታን፣ ኪርጊስታን፣ ተርከሚኒስታን እና አፍጋኒስታን ድረስ ተሰምቷል ነው የተባለው።
በአጠቃላይ የርዕደ መሬቱ ንዝረት የተሰማቸው ሰዎች ቁጥር 285 ሚሊየን እንደሚደርስም ተገምቷል።
ከሰሜን አፍጋኒስታን ባዳክሻን ግዛት የተነሳው ርዕደ መሬት በአፍጋኒስታንም ሆነ በፓኪስታን ያደረሰው ጉዳት እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።
የደቡብ እስያ ሃገራት ከዚህ ቀደምም ከባድ የርዕደ መሬት አደጋዎች ደርሶባቸዋል።
በፓኪስታን በፈረንጆቹ 2005 በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 6 ሆኖ የተመዘገበ አደጋ የ73 ሺህ ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ የሚታወስ ነው።
ባለፈው አመት በአፍጋኒስታን በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋም ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም።