ኃርፕ የተሰኘው የአሜሪካ ከርሰ ምድር ጥናት ማዕከል ለአደጋው መንስኤ ሊሆን ይችላል ተብሎ ተጠርጥሯል
ከ12 ቀናት በፊት በደቡባዊ ቱርክ እና ሰሜናዊ ሶሪያ አካባቢዎች ላይ የደረሰው የርዕደ መሬት አደጋ በገዳይነቱ ከቀዳሚዎቹ አደጋዎች መካከል ተመዝግቧል።
በዚህ አደጋ እስካሁን ከ45 ሺህ በላይ ቱርካዊያን እና ከ6 ሺህ በላይ ሶሪያዊያን ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን አደጋው ብዙዎችን አስደንግጧል።
የአደጋው ተጎጂዎች መብዛታቸውን ተከትሎ ከሁለቱ ሀገራት በተጨማሪ በርካታ ሀገራት እና የረድኤት ተቋማት ለሁለቱም ሀገራት ድጋፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
- ኢትዮጵያ በቱርክ በመሬት መንቀጥቀጥ ለተጎዱ ሰዎች የቁሳቁስና የነፍስ አድን ቡድን መላኳን ጠ/ሚ ዐቢይ አስታወቁ
- የቱርክ እና ሶሪያን ርዕደ መሬት የተነበየው ሆላንዳዊ ቀጣይ ተረኞቹ እነማን ናቸው አለ?
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ይህ ገዳይ የርዕደ መሬት አደጋ እንዴት ሊከሰት ቻለ አደጋው ሰው ሰራሽ ነው እና ሌሎችም መላ ምቶች የቀጠሉ ሲሆን ብዙዎች የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ ከአደጋው ጀርባ አለች ብለው እንደሚያስቡ ተገልጿል።
"ሀርፕ" የተሰኘው የአሜሪካ የከርሰ ምድር ጥናት ማዕከል በፈረንጆቹ 1990 በአሜሪካ ህግ አውጪ የተቋቋመ ተቋም ሲሆን ዓላመውም የመሬትን ውጫዊ ስሪት ለማጥናት በሚል ነበር።
በዚህ የጥናት ተቋም ውስጥ የአሜሪካ አየር ሀይል እና የባህር ሀይል በጋራ ይሰራሉ የተባለ ሲሆን የመሬት ውጫዊ ክፍልን እና ጠፈር መካከል ያለውን ሞገድ ማጥናት ዋነኛ ግቡ ነውም ተብሏል።
ይህ የጥናት ማዕከል በመሬት ክፍል ውስጥ ከ60 እስከ 500 ኪሎ ሜትር ጥልቀት ውስጥ ከፍተኛ ሞገድ መኖሩን በጥናቱ እንደለየ አስታውቋል።
ተቋሙ ጥናቱን ሲያከናውን በከርሰ ምድር ውስጥ ያሉ ኤሌክትሮኖችን ለማሞቅ የራዲዮ ሞገዶችን እንደሚጠቀም ያስታወቀ ሲሆን በዚህ ጊዜ በመሬት የላይኛው ክፍል ላይ መጠነኛ መንቀጥቀጥ ሊያጋጥም እንደሚችል ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም በቱርክ እና ሶሪያ የደረሰው ገዳይ የርዕደ መሬት አደጋ በዚህ የአሜሪካ የከርሰ ምድር ጥናት ማዕከል ምክንያት የተከሰተ ሊሆን ይችላል የሚሉ ሃሳቦች በስፋት ተሰራጭተዋል።
የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት መሳቡን ተከትሎ በጉዳዩ ዙሪያ የመረጃ ማጣራት ስራ ማከናወኑን አስታውቋል።
ኤኤፍፒ ለዚህ መረጃ ማጣራት ስራው የከርሰ ምድር ተመራማሪ እና የሳይንስ ባለሙያዎችን ያነጋገረ ሲሆን የሃርፕ ፕሮግራም ሃላፊ የሆኑት ጀሲካ ማቲው ስለ ቱርክ እና ሶሪያ ርዕደ መሬት መነሻነት ተብሎ እየተነሳ ያለው መረጃ ፈጽሞ ሀሰት እና ሊሆን የማይችል ነው ብለዋል።
በቦስተን ዩንቨርሲቲ የአስትሮኖሚ ፕሮፌሰሩ ጀፍሪ ሁስ በበኩላቸው የሬድዮ ሞገዶች በመሬት የላይኛው ክፍል ላይ መጠነኛ መረበሽን ሊያስከትሉ ይችላሉ ነገር ግን በቱርክ እና ሶሪያ የደረሰውን አይነት ከባድ አደጋ ግን በሰው ሰራሽ መንገድ እንዲከሰት ማድረግ አይቻልም ብለዋል።
ሌላኛው የዚሁ ሙያ ተመራማሪ ቶሺ ኒሺሙራ ደግሞ ርዕደ መሬትን በሰው ሰራሽ መንገድ እንዲከሰት ማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ እስካሁን አለመፈጠሩን ተናግረዋል።
በቱርክ እና ሶሪያ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎችን የገደለው ርዕደ መሬት አደጋ ከዚህ በፊት የከርሰ ምድር ተመራማሪዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥተውበት እንደነበር ነገር ግን ቱርክ የባለሙያዎቹን ምክር ችላ ማለቷን እነዚሁ ተመራማሪዎች አክለዋል።