የቱርኳ አንታክያ ከሦስተኛው ርዕደ መሬት በኋላ ወደ ምድረ በዳነት ተቀየረች
በርዕደ መሬቱ ክፉኛ የተጎዳችው አንታክያ ወደቀደመ ድምቀቷ ለመመለስ አመታትን ትፈልጋለች ተብሏል
በቱርክ የርዕደ መሬት አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ45 ሺህ ተሻግሯል
በሁለት ሳምንታት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰባት የቱርኳ አንታኪያ ከተማ ባዶ ሆናለች።
በድቅድቅ ጨለማ ጎዳናዎች ታጅባ፤ የፍርስራሾችና የተሰባበሩ መስኮቶች መለያዋ ሆነዋል።
በመሬት መንቀጥቀጡ የተረፉት የ50 ዓመቱ መህመት አይ መላው ህይወቱ በአንታክያ ነው። በከተማዋ ከቀሩት ጥቂት ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆነው መህመት "ሁሉም ሰው ሄዷል" ብሏል።
ነዋሪዎች ወይ ሞተዋል ወይ ተሰደዋል ሲልም አክሏል።
"መንገዶቻችን ገነት ነበሩ። በአንድ ምሽት ሁሉም ነገር ወድሟል" ማለቱንም ሬውተርስ ዘግቧል።
"መጠለያችንን መልቀቅ አንችልም። በሄድክበት ቦታ ሁሉ አደገኛ ስለሆነ መዞር ከባድ ነው። ህንፃዎቹ አደገኛ ናቸው። ሳታውቀው በአንተ ላይ ሊፈርስ ይችላል" በማለት ውጣ ውረዱን ተናግሯል።
"አደጋው በሁላችንም ላይ ወደቀ" ያሉት የ57 ዓመቱ የእቃ ማጠቢያ ማሽን ሰሪ፤ ሶሪያን ሸሽተው ለ12 ዓመታት በአንታክያ የሚኖሩት ሳሌም ፋዋኪርጂ ናቸው።
ሁለቱ ሴት ልጆቻቸው እና አንድ ወንድ ልጃቸው በየካቲት ስድስቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍርስራሹ ውስጥ ተርፈዋል።
የበኩር ልጃቸው ግን እድለኛ እንዳልነበር ተናግረዋል።
"ረጅም ጊዜ ይወስዳል፣ ዓመታትን ይወስዳል። ግን እንደገና እንገነባዋለን" ብለዋል የ50 አመቱ መህመት አይ።
"ፈጣሪ ቢፈቅድ ከቀድሞው የተሻለ ይሆናል" በማለትም ተስፋው ፡ ገልጿል።
በቱርክ በፈረንጆቹ የካቲት 6 እና ከሁለት ሳምንት በፊት በደረሱት የርዕደ መሬት አደጋዎች የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ45 ሽህ በላይ መድረሱን ቲ አር ቲ ዘግቧል።