የቱርክ እና ሶሪያን ርዕደ መሬት የተነበየው ሆላንዳዊ ቀጣይ ተረኞቹ እነማን ናቸው አለ?
ፍራንክ ሆገርቤትስ የተባለው ተመራማሪ በሀገራቱ ርዕደ መሬቱ ከመድረሱ ከሶስት ቀናት በፊት ትንበያውን ማጋራቱ የሚታወስ ነው
የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ግን ርዕደ መሬትን መቼና የት እንደሚከሰት በትክክል መተንበይ አይቻልም ብሏል
በቱርክ እና ሶሪያ የደረሰውን ርዕደ መሬት አስቀድሞ የተነበየው ሆላንዳዊ ቀጣይ ስጋት ያለባቸውን ሃገራት ይፋ አድርጓል።
“ሶላር ሲስተም ጂኦሜትሪ ሰርቬይ” በተሰኘ ተቋም የሚሰራው ፍራንክ ሆገርቤትስ በደቡብ ማዕከላዊ ቱርክ፣ ሶሪያ፣ ዮርዳኖስ እና ሊባኖስ ርዕደ መሬት እንደሚከሰት በተነበየ በሶስተኛው ቀን አደጋው ደርሷል።
ሆገርቤትስ በሀገራቱ በሬክተር ስኬል 7 ነጥብ 5 ሆኖ የሚመዘገብ ርዕደ መሬት እንደሚከሰት ተንብዮ የነበረ ሲሆን፥ ከግምቱ እጅግ የተቀራረበ (7 ነጥብ 7 እና 7 ነጥብ 8) አደጋ ነው ያጋጠመው።
ርዕደ መሬቱ ተመራማሪው በጠቀሳቸው ዮርዳኖስ እኛ ሊባኖስ ጉዳት ባያደርስም ንዝረቱ መሰማቱም በትዊተር ገጹ ያጋራውን መረጃ በርካቶች እንዲቀባበሉት ማድረጉን አልአረቢያ አስነብቧል።
ሆላንዳዊው ተመራማሪ በቅርቡ መሰል አደጋ አንዣቦባቸዋል ያላቸውን ሃገራትም በትዊተር ገጹ ላይ አጋርቷል።
አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን እና ህንድ አደገኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሊገጥማቸው ይችላል ያለው ሆገርቤትስ፥ “ግምቴ በፍጹም ትክክል ነው ማለት ባይቻልም በነዚህ ሀገራት አካባቢ የሚታየው እንቅስቃሴ ከበድ ያለ ርዕደ መሬት መከሰቱ እንደማይቀር ያሳያል” ብሏል።
ተመራማሪው እንደሚሰራበት ያስታወቀው “ሶላር ሲስተም ጂኦሜትሪ ሰርቬይ” ከርዕደ መሬት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንደሚያጠና ነው በድረገጹ ያሰፈረው።
ይሁን እንጂ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ሆገርቤትስ ትንበያውን በትዊተር ገጹ ላይ ካሰፈረ በኋላ ፥ “ርዕደ መሬት ይተነበያል ወይ? ቢቻል ኖሮ በቱርክና ሶሪያ ከ33 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ባላለፍ” የሚሉና ሌሎች አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ በሰጠው ምላሽም፥ “ርዕደ መሬትን በዚህ ቀን ይደርሳል ብሎ መተንበይ አይቻልም” ብሏል።
የተቋሙ ተመራማሪዎች በተለያዩ አካባቢዎች በአመታት ውስጥ ሊደርሱ የሚችሉ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎችን ግምት ሊያስቀምጡና የቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ምክረ ሃሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ እንጂ “በዚህ አመት ወይም ወር በዚህ ሀገር ርዕደ መሬት ይከሰታል” ብለው ማስቀመጥ እንደማይችሉም ያክላል፡
ሆላንዳዊው ተመራማሪ ግን በፈረንጆቹ ጥር 29 2023 ህንድ፣ ፓኪስታን እንዲሁም አፍጋኒስታን የቱርክና ሶሪያ እጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው የሚያሳስብ ትንበያውን አጋርቶ በርካቶችም መነጋገሪያ ርዕስ አድርገውታል።