ገናን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያከብሩት ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብጽ፣ ሩስያ እና ዩክሬንን ጨምሮ 14 ሀገራት የገና በዓልን በዛሬው እለት እያከበሩ ነው
የጎርጎሮሳውያኑን የዘመን ቀመር የሚከተሉ ሀገራት ክርስቲያኖች የገና በዓልን ከ12 ቀናት በፊት ማክበራቸው ይታወሳል
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ገና በምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በዛሬው እለት እየተከበረ ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የጁሊያን የዘመን ቀመር የሚከተሉት ሀገራት ናቸው በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊስነስርአቶች በዓሉን እያከበሩ የሚገኙት።
ከአለማችን ህዝብ 12 ከመቶው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን መሆኑን ታይም መጽሄት ይዞት በወጣው መረጃ ያመላክታል።
ከ250 እስከ 300 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነትን እንደሚከተሉም ነው ግምቱን ያስቀመጠው።
በምስራቅ አውሮፓ፣ መከከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ከፍተኛ የእምነቱ ተከታዮች ቁጥር ይገኝባቸዋል።
የዘመን ቀመሯን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋር ያዋደደችው ኢትዮጵያ 2015ኛውን የልደት በዓል እያከበረች ነው።
በዓሉ በተለይም በላሊበላ የወትሮ ድምቀቱን ይዞ የተከበረ ሲሆን፥ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮችም ከሁለት አመት በኋላ በሰላም ማክበር ችለዋል።
ከ15 ሚሊየን በላይ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አማኞችም የገና በዓልን በዛሬው እለት እያከበሩት ነው።
ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤል ሲሲም ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፥ ግብጻውያን ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ሰላማዊነትን፣ መቻቻል፣ ይቅርታ እና ለጋስነትን ሊማሩ ይግባል ብለዋል።
በሩሲያም የገና በዓል ዋዜማን በጾም የሚያሳልፉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በዛሬው እለት የገና በዓልን በማክበር ላይ ናቸው።
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም እንደወትሯቸው ህዝብ በተሰበሰበበት ባይሆንም በክሬምሊን በሚገኝ ካቴድራል የቅዳሴ ስርአት ላይ መገኘታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።
ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ያሉት ፑቲን፥ በዓሉን አስመልክተው የ36 ስአት የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጃቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ኬቭ የተናጠል የተኩስ አቁሙ “የይስሙላ” ነው በሚል የተቃወመችው ሲሆን፥ ጦርነቱ ስለመቀጠሉ እየተዘገበ ነው።
ዩክሬናውያን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በዓሉን በስጋት ውስጥም ሆነው በማክበር ላይ ናቸው።
የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓሉን እንደ ምዕራባውያኑ በታህሳስ 25 ማክበር ለሚፈልጉ ምዕመናን ፈቃድ መስጠቷ ይታወሳል።
የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያናት በሚገኙባቸው ኤርትራ፣ እስራኤል፣ አርመኒያ፣ ሰርቢያ፣ ቤላሩስ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ቡልጋሪያ፣ መቄዶኒያ፣ ጆርጂያ እና ሞልዶቫም የገና በዓል በዛሬው እለት እየተከበረ ነው።
የጎርጎሮሳውያኑን የዘመን ቀመር የሚከተሉ ክርስቲያኖች ከ12 ቀናት በፊት የገና በዓልን ማክበራቸው ይታወሳል።