የሩሲያው ፕሬዝዳንት በገና በዓል ምክንያት “የተናጠል የተኩስ አቁም” ትእዛዝ አስተላለፉ
የተናጠል ተኩስ አቁሙ ከዛሬ አርብ ጀምሮ ለ36 ሰአታት የሚቆይ ነው ተብሏል
የፑቲን የተኩስ አቁም ጥያቄ በኪቭ ባለስልጣናት በኩል ውድቅ ተደርጓል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን የሚገኙ ወታደሮቻቸው የገና በዓል እንዲያከብሩ በሚል ለ36 ሰአታት የሚቆይ የተናጠል የተኩስ አቁም ትእዛዝ አስተላለፉ፡፡
ተኩስ አቁሙ ከዛሬ አርብ 6፡00 (በሞስኮ ሰዓት አቆጣጠር 12፡00 ሰዓት) የሚጀምር መሆኑም ነው የተገለጸው፡
ፑቲን በዩክሬን በኩል ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፑቲን ዩክሬንም በጉዳዩ ላይ መልስ እንድትሰጥ ጥሪ ያቀረቡት ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የገና በዓል ዋዜማን እና ነገ የሚከበረውን የገና በዓልን ማክበር ይችላሉ በሚል መሆኑም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
"ኦርቶዶክስ ነን የሚሉ በርካታ ዜጎች እኛን በጠላትንት የፈረጁ በመሆናቸው ከእኛ ይልቅ የዩክሬይን ወገን የተኩስ አቁም አዋጅ እንዲያውጅና በገና ዋዜማ እንዲሁም በእለቱ አገልግሎቶች ላይ እንዲገኙ እድል እንዲሰጣቸው” ሲሉም ጠይቀዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ይሁን እንጅ ከ10 ወራት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ የመጣው የፑቲን ጥያቄ፤ በኪቭ ባለስልጣናት በኩል ውድቅ ተደርጓል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በሰጡት መግለጫ፤ "ፑቲን ገናን እንደ ሽፋን በመጠቀም በዶንባስ በኩል ያለው የወታደሮቻችንን ግስጋሴ ለማስቆም እና መሳሪያዎችንና ጥይቶችን ለማቅረብ እንዲሁም ወደ ቦታችን ለመቅረብ እየሞከረ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ ሩሲያ ጦርነቱን በአዲስ መልክ ለማስፋፋት የምትጠቀምበት ዘዴ መሆኑ ዓለም ሁሉ የሚያውቀው ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ሌሎች የዩክሬን መሪዎችም በበኩላቸው የፑቲንን ርምጃ የፕሮፓጋንዳ ዘዴ እና ሞስኮ ወታደራዊ ኃይሏን እንደገና ለማሰባሰብ ተጨማሪ ጊዜ ለመግዛት የምታደርገው ሙከራ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
የኪቭ ባለስልጣናት ይህን ይበሉ እንጅ የፑቲን ትእዛዝ የመጣው ጦርነቱ በመቆሙ ሳይሆን፤ ፕሬዝዳንቱ ከሩሲያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪ የቀረበላቸውን ጥሪ ስለተቀበሉ መሆኑን የክሬምሊን መግለጫ ያመለክታል፡፡
የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የገናን በዓል በጁሊያን አቆጣጠር ታህሳስ 29 እንደምታከብር ይታወቃል፡፡
በዩክሬን የሚገኙ አንዳንድ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በሞስኮ ላይ ያላቸውን ቁጣና እምቢተኝነት ለማሳየት ታህሳስ 25 ቀን የገናን በዓል ማክበር ጀምረዋል።