ፊፋና የአውሮፓ እግርኳስ ማህበርን ያስቆጣው የአውሮፓ እግርኳስ ገላጋይ ፍርድቤት ውሳኔ
ፍርድቤቱ “የአውሮፓ ሱፐር ሊግ”ን በሚቀላቀሉ ክለቦች ላይ የሚተላለፍ ቅጣት ህገወጥ ነው የሚል ውሳኔ አሳልፏል
12 ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች በ2021 አዲሱን “የአውሮፓ ሱፐር ሊግ” ውድድር ለመቀላቀል መስማማታቸው ይታወሳል
በአዲስ መልክ ይመሰረታል የተባለውን “የአውሮፓ ሱፐር ሊግ” በሚቀላቀሉ ክለቦች ላይ የሚወሰድ እርምጃ ህጋዊ አይደለም ሲል የአውሮፓ የእግርኳስ ገላጋይ ፍርድቤት ውሳኔ ሰጥቷል።
ፍርድቤቱ ይህን ውሳኔ ያሳለፈው “የአውሮፓ ሱፐር ሊግ” እና የሚቀላቀሉት ክለቦች ክስ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው።
የአለም እግርኳስ ማህበር (ፊፋ) እና የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር፥ “የአውሮፓ ሱፐር ሊግ” ውድድርን በሚቀላቀሉ ክለቦች ላይ ማዕቀብ እንጥላለን ማለታቸው ይታወሳል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እና የሚቀላቀሉትን ክለቦች ቅሬታ የተመለከተው የአውሮፓ የእግርኳስ ገላጋይ ፍርድ ቤትም ፊፋ እና የአውሮፓ እግርኳስ ማህበርን ያስቆጣ ውሳኔ በዛሬው እለት አሳልፏል።
ፍርድቤቱ አዲሱን ውድድር በሚቀላቀሉ ቡድኖች ማገድ ህገወጥ ነው ያለ ሲሆን፥ ለአውሮፓ ሱፐር ሊግ መስራቾች መልካም የምስራች ነው ተብሏል።
ውሳኔው የአውሮፓ ሱፐር ሊግ እንዲቋቋም የሚፈቅድ ባይሆንም የአለማቀፉንና የአውሮፓ እግርኳስ አስተዳዳሪዎች የእርምጃ እንወስዳለን ዛቻ የሚቀንስ ይሆናል።
ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድን ጨምሮ አዲሱን ሊግ ለመቀላቀል የወሰኑ ክለቦች የፍርድቤቱን ውሳኔ አድንቀዋል።
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ የውድድር ፕሮጀክት “ራስ ወዳድ ክለቦች የተሰባሰቡበት ነው” ያለው የስፔን ላሊጋ በበኩሉ የፍርድቤቱን ውሳኔ ተቃውሞታል።
“የአውሮፓ ሱፐር ሊግ” ምስረታና ታላላቅ ክለቦች
የአውሮፓ ሱፐር ሊግ የውድድር ሃሳብ በሚያዚያ ወር 2021 ይፋ ሲደረግ ስድስት የእንግሊዝ ክለቦችን ጨምሮ 12 የአውሮፓ ታዋቂ ክለቦች ሊቀላቀሉት መስማማታቸው ይታወሳል።
በአዲሱ ሊግ ከእንግሊዝ አርሰናል፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ ቼልሲ እና ቶተንሀም፤ ከጣልያን ኤሲ ሚላን፣ ኢንተር ሚላን እና ጁቬንቱስ፤ ከስፔን ደግሞ ሪያል ማድሪድ፣ ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድ ለመሳተፍ ስምምነት ላይ መድረሳቸውም አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ ከደጋፊዎች፣ ከፊፋ እና ከሀገራት መሪዎች ጭምር ተቃውሞው ሲበረታ በ72 ስአት ውስጥ እቅዱ ወደ መክሰም ተቃርቦ ነበር።
የአውሮፓ እግርኳስ ማህበርም በስድስቱ የእንግሊዝ ክለቦች እንዲሁም በአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ኢንተርሚላን እና ኤሲ ሚላን ላይ ቅጣት መጣሉና ጁቬንቱስም ከዚህ ፕሮጀክት ለመውጣት መወሰኑን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
የፊፋ እና የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር የእገዳ ዛቻው ቢቀጥልም የአውሮፓ ሱፐር ሊግን የመጀመር ውጥኑ ሙሉ በሙሉ አልተሰረዘም፤ ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ በተለይ በውድድሩ የመሳተፍ ከፍ ያለ ፍላጎት አላቸው ተብሏል።
“የአውሮፓ ሱፐር ሊግ” ውድድር ምን ልዩ ያደርገዋል?
ሊጉ 20 ተሳታፊ ቡድኖችን ያካተተ ውድድር ለማዘጋጀት ውጥን ይዞ ነው የተነሳው።
12ቱ መስራች ክለቦች እና ሶስት ተጨማሪ ክለቦች ተቀላቅለውት ከአገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች ደግሞ አምስት ቡድኖች ተወዳድረው ይጨመራሉ የሚል እቅድም ይዞ ነበር።
ውድድሩ በየዓመቱ ነሀሴ ወር ላይ እንዲካሄድና ጨዋታዎችም በሳምንቱ አጋማሽ ላይ እንዲደረጉ መታቀዱ ይታወሳል።
ተሳታፊዎቹ 20 ቡድኖች በሁለት ምድቦች ተከፍለው በደርሶ መልስ ጨዋታ እንደሚፋለሙም መገለጹ አይዘነጋም።
በመጀመሪያዎቹ የውድድር ወራት እስከ 10 ቢሊየን ዩሮ ያስገኛል ተብሎ የነበረው ውድድር በኮሮና ወረርሽኝ ክፉኛ ለተጉዱት ክለቦች ገቢያቸውን እንደሚያሳድግላቸው ተነግሯቸዋል።
ከገቢው ባሻገር ፉክክርን የሚያሳድግ አዲስ የውድድር መርሃግብር መጀመሩ ለአውሮፓ እግርኳስ እድገትም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ከአውሮፓ ሱፐር ሊግ አዘጋጆች ሲገለጽ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የጋላክቲኮዎቹ ውድድር እንደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ያሉ ሰፊ አለማቀፍ ተከታታይ ያላቸውን ውድድሮች ሊያደበዝዝ ይችላል የሚሉ ስጋቶች ከስፖርት ቤተሰቡ ተነስተዋል።
መስራቾቹን ክለቦች አይነኬ የሚያደርገው ውድድር ፎርማቱ ለታዳጊ ክለቦች እድል አይሰጥም የሚሉ ትችቶችም ሲቀርቡበት ነበር።
ክለቦች ገንዘብ ለማግኘት ብለው ውድድሩን ለመቀላቀል መወሰናቸው በደጋፊዎቻቸውም እምብዛም የተደገፈ አልነበረም።
ዛሬ የአውሮፓ እግርኳስ ገላጋይ ፍርድቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የአውሮፓ ሱፐር ሊግ ፕሮጀክት ዳግም ማንሰራራቱና መነጋገሪያ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ይመስላል።