እምቦጩን ማጥፋት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በባህር ዳር የምክክር መድረክ ተካሂዷል
የአማራ ክልል ጣናን ከእምቦጭ የመታደጉ ሥራ በፌደራል መንግስት ሊመራ ይገባል አለ
የኢትዮጵያን ትልቁን ሐይቅ ከእምቦጭ አረም የመታደጉ ሥራ በፌደራል መንግስት አስተባባሪነት እና ግንባር ቀደም ተሳትፎ ሊመራ እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ፡፡ ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ መንግስታቸው ከዚህ በፊት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹ ሲሆን በዋናነት ግን የፌዴራል መንግስት ጉዳዩን በግምባር ቀደምትነት ሊመራው ይገባል ብለዋል፡፡
እምቦጩን ለማጥፋት በባህር ዳር በተደረገ የምክክር መድረክ መግባባት ላይ የተደረሰ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተመስገን ጣናን ከእንቦጭ አረም በመታደግ የትውልድ ኃላፊነትን መወጣት ይገባል ሲሉ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ ሐይቁን ከእምቦጭ ለመታደግ የተጀመረው ሥራ ተስፋ ሰጭ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ከፍፃሜ ማድረስ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎች ሐይቁን ከተጋረጠበት አደጋ የማዳኑን ሥራ በተመለከተ የፌዴራል መንግስት ትኩረት እንዳልሰጠው የተለያዩ አካላት እያነሱ ናቸው፡፡
የጣና ሐይቅ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት እየደረሰበት እንደሆነ እንዲሁም የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ትኩረት እንዳልሰጡት የጣና ሐይቅና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አያሌው ወንዴ ለአል ዐይን ከዚህ ቀደም ገልጸው ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አል ዐይን አማርኛ በፌዴራል መንግስት ደረጃ የሚመለከተውን በውኃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣንን ጠይቋል፡፡ የጣና ሐይቅን ከእምቦጭ የመታደግ ሥራን የፌዴራል መንግስት “ትኩረት አልሰጠውም” የሚለውን ትችት እንደማይቀበል ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡
የባለሥልጣኑ የኢኮ ሐይድሮሎጂ ዳይሬክተር ዮሐንስ ዘሪሁን “የፌዴራል መንግስት ዝም አለ፤የሚጠበቅበትን ስራ አልሰራም ፤ የሚለውን ወቀሳ ብዙ ጊዜ የማንቀበለውና የተሳሳተ አባባል ነው” ሲሉ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡ ከዛሬ ዓመት በፊት ከባለሙያዎችና ከሚመለከታቸው ጋር ለምን ውጤት እንዳልተገኘ ዉይይት መደረጉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ የቅንጅት አለመኖሩ ግን ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
የእምቦጭ አረሙን ለመቆጣጠር ጥረቶች እንደነበሩ ያነሱት አቶ ዮሐንስ ይህ ግን በትብብር ቢሆን የተሻለ እንደነበር አንስተዋል፡፡ የአረሙን ማጥፋት በተመለከተ ስትራቴጂክ ዕቅድ እንዳልነበረም ነው አቶ ዮሐንስ ያብራሩት፡፡ ይሁንና አሁን ላይ የተሻለ ትብብር በመፍጠር እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡
እምቦጭ አረም የጣና ሐይቅን 4ሺ ሄክታር ሸፍኖ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን 1 ሺ ሄክታር የሚሆነው የሐይቁ ክፍል በአረሙ መወረሩ ተገልጿል፡፡
በርካቶች አሁንም የጣና ሐይቅ ከእምቦጭ አረም የሚላቀቅበትን ጊዜ ይጠብቃሉ፡፡