ኮርፖሬሽኑ የገንዘብ ችግሩን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አሳውቆ እንደነበር ገልጾ ከመንግስት የበጀት ድጎማ ጠይቋል
ኢቢሲ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው ገለጸ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በገቢ ራሱን እንዲችል ከተወሰነ በኋላ አሁን ላይ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው ገልፀ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ንጉሴ ምትኩ (ዶ/ር) ለአል-አይን አማርኛ እንደገለጹት “በየወሩ ለደመወዝና ለሥራ ማስኬጃ ብቻ ከ45 እስከ 46 ሚሊዮን ብር ወጪ” እያደረገ ያለው ኮርፖሬሽኑ በመንግስት በጀት መደገፉ ስለቆመ የገንዘብ እጥረት ውስጥ ገብቷል፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) በ2006 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 858/2006 በኮርፖሬሽን ደረጃ ሲዋቀር፣ መንግስት በቀጥታ የሚበጅትለት በጀት ቀርቶ ከማስታወቂያና ከስፖንሰርሺፕ በሚያገኘው ገቢ ራሱን እንዲችል ተደርጎ ነበር፡፡
ነገርግን ዋና ስራ አስፈፃሚው ዶ/ር ንጉሴ ፣ ኢቢሲ ትልቅ ተቋም በመሆኑ በራስ የገንዘብ አቅም ማስተዳደር ከባድ እንደሆነና ፣ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርግለት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ ቀድሞ የሚያደኘው ገቢ በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ በማድረግ ተጨማሪ ፈተና ሆኗል፡፡
ቀደም ሲል ለሳተላይት ፣ ለቴሌና ለመብራት ኃይል ክፍያዎች መንግስት ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አሁን ላይ ግን ይህ ድጋፍ መቆሙን ተናግረዋል፡፡
ንጉሴ ምትኩ (ዶ/ር)
ኮርፖሬሽኑ ለደሞዝና ለሳተላይት ክፍያ የሚውል የ191 ሚሊዮን ብር ድጎማ እንዲሰጠው በአዋጁ መሰረት ሚያዝያ 27/2012 ለገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረቡን የኮርፖሬሽኑ የፋይናንስ ዘርፍ ዲቪዥን ኃላፊ አቶ ተፈራ ቶሌራ ለአል-አይን በስልክ ገልጸዋል፡፡ የድጎማ ጥያቄውን በተመለከተ ያናገርናቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ጉዳዩን አይተን ጊዜው ሲደርስ ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ንጉሴ ምትኩ (ዶ/ር) ”የቀድሞው አዋጅ መሻሻል አለበት ፤ አዋጁን አዘጋጅተን ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ልከነዋል ፤ እነርሱ ቅርጽ እየሰጡት ነው ፤ ከዚያ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይላካል፡፡ ያኔ ብዙ ነገሮች እንደሚቀየሩ ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የማሻሻያው ዓላማ በአዋጁ መንግስት ለኮርፖሬሽኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቢገለጽም ድጋፉን ማን እንደሚሰጥ በግልጽ በለመቀመጡ ይህ እንዲስተካከል የሚጠይቅ ነው፡፡
“የቴሌቪዥን ፈቃድም ቢሆን አሰባሰቡ ችግር አለበት፡፡ ነገር ግን ከመብራት ወይም ከውሃ ጋር ከተሰበሰበ ትልቅ ገንዘብ ይሆናል” ብለዋል ዶ/ር ንጉሴ፡፡
በየቦታው ከ100 በላይ ትራንስሚተር እንዳለ የሚገልጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የካፒታል የሥራ ማስኬጃ በጀት የለውም ይሄ ይሄ ከአወቃቀሩ ጋር የሚያያዝ ነው ያሉ ሲሆን ይህንን ለማስረዳት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ጉዳዩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም፣ ለቦርድም ቀርቧል ያሉት ዶ/ር ንጉሴ በቅርቡ ይስተካከላል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ስራ አስፈፃሚው እንዳሉት ኢቢሲ የራሱን ገቢ ለማግኘት ባደረገው ጥረት በ2012 ዓ.ም ብቻ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ ይሁንና በየጊዜው ከሚወጣው ወጪ እና ከወቅቱ አንጻር ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ንጉሴ ገለጻ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲያውቁት የተደረገ ሲሆን ችግሩ እንደሚፈታ ያላቸውን እምነት አንስተዋል፡፡
የተቋሙ የገንዘብ እጥረት ከተፈታ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖርባቸው የአረብ ሃገራት፣ አሜሪካና አውሮፓ ዘጋቢዎች እንዲኖሩ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡
የቀድሞው የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሥዩም መኮንን መንግስት ተቋሙን በበጀት እንዲደግፍ ጥያቄዎችን ስለማቅረባቸው የተቋሙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ኢቢሲ ያጋጠመው የገንዘብ ችግር እንደሚያሰጋቸው እና “መንግስት በአፋጣኝ የማይደጉመው ከሆነ ይህ አንጋፋ የሀገር ተቋም የከፋ ችግር ሊገጥመው ይችላል” የሚል ስጋት እንዳለባቸውም ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የተቋሙ ሰራተኞች ለአል-አይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ2,000 በላይ ሰራተኞች ያሉት ኮርፖሬሽኑ ሶስት የቴሌቪዥን ቻናሎችን (ኢቲቪ ዜና፣ ኢቲቪ መዝናኛና ኢቲቪ ቋንቋዎች) ፣ ሦስት የሬዲዮ ጣቢያዎችን (ኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ኤፍ እም አዲስ 97 .1 እና ኤፍ ኤም 104.7) እንዲሁም አዲሱን ሚዲያ ያስተዳድራል፡፡