በአዲስ አበባዋ ገርጂ አካባቢ የሚኖሩት የ65 ዓመቷ የወ/ሮ ስንዱ ሰውነት መውለድ አነጋጋሪ ሆኗል
የ65 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ማርገዛቸውን ሳያውቁ ወንድ ልጅ በምጥ መገላገላቻ ተሰማ
ልጅ ወልዶ ለመሳም ባለመታደላቸው ፈጣሪያቸው ልጅ እንዲሰጣቸው ሌት ተቀን ሲማፀኑ መኖራቸውን የገለጹት ወ/ሮዋ በኋላም ተስፋ መቁረጣቸውን ገልጸው 'የወር አበባ ማየት ካቆምኩኝ ረጅም ጊዜ ተቆጥሯል' ሲሉም ከወለዱ በኋላ ተናግረዋል፡፡
ግንቦት 16 ቀን 2012 ዓ.ም “ሆዴን አሞኛል፣ ይቆርጠኛል” ሲሉ ወደስራቸው ለሄዱት ባለቤታቸው በስልክ መንገራቸው ተገልጿል፡፡ የተለመደ የጨጓራ ህመም እንዳለባቸው የሚያውቁት ባለቤታቸው "ፈሳሽ ነገርም አየሁ" ሲሏቸው ጎረቤቶቻቸው ወደ ጤና ጣቢያ እንዲወስዷቸው መጠየቃቸውንና ጎረቤቶችም ወይዘሮ ስንዱን ገርጂ አካባቢ ወደሚገኘው ድል ፍሬ ጤና ጣቢያ እንደወሰዷቸው የኢዜአ ዘገባ ያሳያል፡፡
ወ/ሮ ስንዱ ሰውነት-ኢዜአ
የጤና ጣቢያው የሕክምና ባለሙያዎች ምርመራ ካደረጉ በኋላ ወይዘሮዋ ነፍሰ ጡር እንደሆኑና ህመሙም ምጥ እንደሆነ በማስረዳት ዘጠኝ ወር ሙሉ ለምን የሕክምና ክትትል እንዳላደረጉ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው ነው የተገለጸው፡፡
ወ/ሮ ስንዱም "ነብሰ ጡር መሆኔን አላውቅም ነበር" ሲሉ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ በዚህ ጊዜ የድል ፍሬ ጤና ጣቢያ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል የላካቸው ወይዘሮ ስንዱ በዘውዲቱ ሆስፒታል ማዋለጃ ክፍል ወንድ ልጅ በምጥ ተገላግለዋል ተብሏል፡፡
ይሄኔ የወይዘሮ ስንዱን ነብሰ ጡርነት ብሎም በዚህ ዕድሜያቸው መውለድ ግርምት የፈጠረባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ወንድ ልጃቸውን የታቀፉት ወይዘሮ ስንዱ ስለ ነብሰጡርነታቸው የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረና በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ በመሆኑ እስከወለዱበት ዕለት ድረስ ከባድ ስራዎችን ይሰሩ እንደነበር ነው የተናገሩት።
ስለ ባለቤታቸው እርግዝና የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረ የገለጹት ባለቤታቸው አቶ ሀብታሙ ገላን ሳያስቡት አባት በመሆናቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
የተወለደው ልጅ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡
የእኚህ ሴት ልጅ የማግኘት ጉጉት የጎረቤቶቻቸውን ልጆች እንደራሳቸው ልጆች እንዲንከባከቡ አድርጓቸዋል። ከልጆች ጋር ያላቸው ቅርበትም የልጆቹን ልዩ ፍቅር አስገኝቶላቸዋል ይላሉ ጎረቤቶቻቸው፡፡ በዚህ ዕድሜያቸው መውለዳቸውን "የፈጣሪ ድንቅ ስጦታ ነው" ሲሉም ጎረቤቶቻቸው ገልጸዋል።
የሴት ልጅ ዕድሜ የመውለድ ዕድልን የሚወስን አንድ መስፈርት ስለመሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የሴቶች ከፍተኛ የመውለድ ዕድል በአሥራዎቹ መጨረሻና በ20ዎቹ መገባደጃ መካከል ሲሆን በ30ዎቹ ዕድሜ ላይ የመራባት ወይንም የማርገዝ ዕድል ማሽቆልቆል እንደሚጀምር በህክምና ይጠቀሳል።
በ45 ዓመት ዕድሜያቸው የመራባት ችሎታ በጣም እየቀነሰ የሚመጣ በመሆኑም ለአብዛኞቹ ሴቶች ማርገዝና መውለድ የማይቻል እንደሆነም ጥናቶች ያሳያሉ።
ይሁን እንጂ ከመቶ አንድ የሚሆን እርግዝና በ50 እና ከዚያ በላይ የዕድሜ ክልል ባሉ ሴቶች ሊያጋጥም እንደሚችልም ነው ጥናቶች የሚጠቁሙት።
በቅርቡ ሕንዳዊቷ የ73 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ መንታ ልጆችን መውለዳቸው፤ በናይጄሪያም የ68 ዓመት ሴት በተመሳሳይ መንታ ልጆችን መገላገላቸው ዓለምን ያስደመሙ ድንቃድንቅ ዜናዎች ነበሩ።