መስማት ለተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን የተለየ ‘ማስክ’ በመስራት ላይ ነው ተባለ
ኮሮና ቫይረስ እና መስማት የተሳናቸው በኢትዮጵያ
ዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሰው ልጆች ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ለተለያዩ የአካል ጉዳቶች የተዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ተጽእኖው ይበረታባቸዋል፡፡
ከአካል ጉዳተኞች መካከል የሆኑት መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በንግግር ወቅት ከሚጠቀሙት የምልክት ቋንቋ በተጨማሪ የከንፈር እንቅስቃሴንም በማንበብ ነው ተግባቦት የሚፈጥሩት፡፡ ይሁንና አሁን ላይ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የሚደረገው መደበኛው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) የተግባቦት ሳንካ በመሆን መስማት ለተሳናቸው ተጨማሪ ችግር ፈጥሯል፡፡
ከኢትዮጵያ ህዝብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑት መስማት የተሳናቸው እንደሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃን በመጥቀስ የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ይገልጻል፡፡ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትዕግስት አለማየሁ እንደሚሉት በሀገሪቱ ለሚገኙ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የፈጠረው ተጽእኖ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡
በሀገሪቱ መስማት ለተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የትምህርት ተደራሽነት እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ባጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ መስማት ለተሳናቸው በማህበሩ የተገነባ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት አንድ ብቻ በአዲስ አበባ እንደሚገኝ ወ/ሮ ትዕግስት ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ቁጥር እጅግ ጥቂት የሚባል ነው፡፡
ወ/ሮ ትዕግስት አለማየሁ
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር ከተመሰረተ በሚቀጥለው ዓመት 2013 ዓ.ም 50 ዓመቱን ይደፍናል፡፡ ማህበሩ ባለፈው ከ49 ዓመት በላይ እድሜው በመላ ሀገሪቱ 27 ቅርንጫፎችን በመክፈት መስማት ለተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱ የምልክት ቋንቋ ማስተማር ነው፡፡ ይሁንና ይሄም ትምህርት ቢሆን ለሁሉም ተደራሽ አይደለም፡፡
መደበኛ ትምህርት እና የምልክት ቋንቋ ላልተማሩ በርካታ መስማት የተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ለተግባቦት የአፍ እንቅስቃሴን መከታተል ከፍተኛ እገዛ አለው፡፡
በአሁኑ ወቅት እንደ ባንክ፣ የጤና ተቋማት እና መሰል አገልግሎት ሰጪ ማህበራዊ ተቋማት መስማት የተሳናቸው አገልግሎት ለማግት በሚሄዱበት ወቅት ፣ አገልግሎት ሰጪ ግለሰቦች ማስክ አድርገው የሚያስተናግዱ በመሆናቸው ፣ ለመግባባት እየተቸገሩ እንደሆነ ወ/ሮ ትዕግስት አጫውተውናል፡፡ ታክሲ ለመሳፈርም ቢሆን መስማት የተሳናቸው በዋናነት የረዳቶችን የከንፈር እንቅስቃሴ በማንበብ ረዳቱ የሚጠራበትን የታክሲዉን አቅጣጫ እንደሚረዱ የገለጹት ወ/ሮ ትዕግስት ረዳቶች መደበኛውን ማስክ አድርገው በሚጠሩበት ወቅት ግን ወዴት እንደሚጭኑ ለማወቅ ያስቸግራል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ማህበሩ ከአንዲት የልብስ ስፌት ዲዛይነር ጋር በመነጋገር አፍ ላይ የሚያርፈው መሀለኛው የ ‘ማስክ’ ክፍል የአፍ እንቅስቃሴን እንዲያሳይ ሆኖ በላስቲክ የተበጀ አዲስ የ ‘ማስክ’ አይነት ለማስሰራት በጥረት ላይ ይገኛል፡፡ መስማት የተሳናቸው እና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚሰሩ ሰዎች አዲሱን የማስክ አይነት በመጠቀም የተሻለ ተግባቦት መፍጠር ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ለዚህም ከጤና ሚኒስቴር ጋር ማህበሩ በትብብር እየሰራ ቢሆንም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም እገዛ እንዲያደርጉ ወ/ሮ ትዕግስት ጠይቀዋል፡፡
ስለ ኮሮና ቫይረስ እና ሌሎችም ጉዳዮች በሚዲያዎች የሚተላለፉ መረጃዎች መስማት ለተሳናቸው የመድረስ እድላቸው ዝቅተኛ ስለሆነ መስማት ለተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሌሎች አማራጮች ሊታሰቡ እንደሚገባም ነው የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ያሳሰቡት፡፡ ከሚዲያ አይነቶች አንዱ የሆነው ሬዲዮ መስማት ለተሳናቸው ተደራሽነቱ ያለ ምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ምንም ትርጉም የሌለው ሲሆን የቴሌቪዥን ስርጭት ያላቸው አንዳንድ ሚዲያዎች ከኮሮና መከሰት ወዲህ በአስተርጓሚዎች መረጃ ማድረስ መጀመራቸው መልካም ጅምር ነው፡፡ ይሁንና ይሄም ቢሆን በኮሮና ቫይረስ መረጃዎች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው ያሉት ወ/ር ትዕግስት ሌሎች መረጃዎችም መስማት ለተሳናቸው እንዲደርሱ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ የትርጉም ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ለሚዲያ ተቋማት ማህበራቸው ሊያቀርብ እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡
መስማት ለተሳናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን ማስክ ትኩረት ሰጥቶ በመስራትም ይሁን መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ረገድ በበለጸጉት ሀገራት የተሻሉ ተግባራት ቢኖሩም ነገር ግን ተጨማሪ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡