ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ያላቸውን አለመግባባት ለመፍታት ድርድር ከጀመሩ አመታት አስቆጥረዋል
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አልጀርስ የገቡት የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ከአልጀሪያው አቻቸው ጋር በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ መወያየታቸው ተገለጸ፡፡
ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው የሕዳሴ ግድብ አሞላል እና አስተዳደር ዙሪያ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት መደረሱ ጠቃሚ እንደሆነ መስማማታቸው ተሰምቷል፡፡
የግብጹ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ፋታህ አል ሲሲ እንደገለጹት የግብጽ የውሃ ደህንነት ጉዳይ የአረብ ብሄራዊ የደህንነት አካል ስለሆነ የግብጽን የውሃ ደህንነት ማስጠበቅ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ተስማምተናል ብለዋል፡፡
የአልጀሪያ ፕሬዝዳንት አብዱል መጅድ ታቦን ግብጽ በህዳሴው ግድብ ፍትሃዊ አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የተሟላ ስምምነት ላይ ለመድረስ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁ መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
የአልጀሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላማምራ በኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን በቀጣይ ሊቀመንበር በምትሆንበት የዐረብ ሊግ ላይ ስለሕዳሴ ግድብ ሚዛናዊ ውይይት እንደምታደርግ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
አልጀሪያ የዐረብ ሊግ ቀጣይ ሊቀመንበር ናት፡፡
ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ባለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሶስትዮሽ ድርድር ማድረግ ከጀመሩ ወደ አስር አመት ሊሆነው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ለልማት መሆኑን እና በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ የጎላ ተጽእኖ እንደማያሳድር በተደጋጋሚ ስትገልጽ፣ ግብጽ ባአንጻሩ የምታገኘው የውሃ ድርሻ እንደሚቀንስና የወሃ ደህንነቷን ስጋት ውስጥ እንደሚከተው ትገልጻለች፡፡