ኢትዮጵያ እና ግብጽ ከህዳሴው ግድብ ባለፈ የትብብር አጀንዳዎቻቸውን ማስፋት እንዳለባቸው ተገለጸ
ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብር ማእቀፍ ስምምነት ወደ አስገዳጅ ህግነት እንዲቀየርም መስራት አለባትም ተብሏል
አዲሱ መንግስት ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር ተጨማሪ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን እንዲያደርግም ተጠይቋል
ኢትዮጵያ እና ግብጽ ከህዳሴው ግድብ ባለፈ የትብብር አጀንዳዎቻቸውን ማስፋት እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ፡፡
በየመን የቀድሞ የኢትዮጵያ አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሂ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ኢትዮጵያ እና ግብጽ ከህዳሴው ግድብ ባለፈ የትብብር አጀንዳዎቻቸውን ማስፋት አለባቸው ብለዋል፡፡
“ሁለቱ አገራት በጋር ሊሰሩባቸው የሚችሉ ጉዳዮች አሉ”ያሉት አምባሳደር ቶፊቅ ሀይማኖትን ጨምሮ የህዝብ ለህዝብ፣ የማህበራዊ እና የንግድ እንዲሁም ሌሎች ክልላዊ እና ዓለምአቀፋዊ ጉዳችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የህዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪና አማካሪ ሆነው ተሸሙ
ሁለቱ አገራት ትግላቸውን በህዳሴ ግድቡ ላይ ብቻ ሊያደርጉ ባይገባም የግብፅ ወንዙን ብቻዬን አጠቀማለሁ በሚል የምታደርገው ጥረት ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ዘለቄታዊ ጥቅሟን የምታረጋግጠው ከ11 አመት በፊት በዩጋንዳ ኢንቴቤ የተፈረመው የናይል ተፋሰስ ሃገራት የትብበር ማእቀፍ (ሲ ኤፍ ኤ) ስምምነት በፈራሚዎቹ አገራት አስገዳጅ ህግ እንዲሆን ስታደርግ ነውም ብለዋል አምባሳደር ቶፊቅ፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ 11 አባላት ያሉት የናይል ተፋሰስ አገራት ማእቀፍ ይህንን ጠቃሚ ስምምነት ያልፈረሙት እንዲፈርሙ እና የአገራቸው አስገዳጅ ህግ እንዲያደርጉት ግፊት ማድረግ እንዳለባት አሳስበዋል፡፡
ማዕቀፉን ከግብፅ፣ሱዳን እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ ዉጪ ያሉት ቀሪዎቹ የተፋሰሱ አገራት ቢፈርሙትም ህግ አድርገው አላጸደቁትም፡፡ ኢትዮጵያ፣ ታናዛኒያ፣ ሩዋንዳ እና ቡሩንዲ ብቻ ናቸው ስምምነቱን ያጸደቁት፡፡
ይህንን ስምምነት ከ11 የተፋሰሱ አባል አገራት መካከል ሁለት ሶስተኛ አባል አገራት በአገራቸው የህግ አፅዳቂ ተቋም ካፀደቁት አሰገዳጅ ህግ ይሆናል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በህዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች መክፈቻ ንግግራቸው ላይ በተያዘው አመት የዲፕሎማሲ ስራው ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ማለታቸው እንዳስደሰታቸውም አምባሳደር ቶፊቅ ተናግረዋል፡፡
“በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከማንም ጋር ምንም አይነት ድርድር አይኖርም”- ፕሬዝዳንት ሣሕለ ወርቅ
በዚህም መሰረት አዲስ የተመሰረተው መንግስት ለአፍሪካ ቀንድ እና መካከለኛው ምስራቅ አካባቢዎች ትኩረት እንዲሰጥም አሳስበዋል፡፡
በተለይም ምስራቅ አፍሪካ የብዙ የአለማችን አገራትን ትኩረት እየሳበ ያለ ቀጠና እየሆነ ነው የሚሉት አምባሳደሩ ኢትዮጵያ የዚህ ክስተት ተመልካች ልትሆን አትችልም ሲሉ አክለዋል፡፡
በመሆኑም የነዚህን አገራት ፍላጎት በመረዳት ብሄራዊ ጥቅማችንን ማስጠበቅ የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ከጎረቤት እና ከተፅእኖ ፈጣሪ አገራት ጋር መወዳጀት በጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከሚመራው አዲሱ መንግስት ይጠበቃል ብለዋል አምባሳደር ቶፊቅ፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ከኢንቨስትመንት፣ ከስራ እድል ፈጠራ፣ ከንግድ እና ሌሎች ጥቅሞች አንጻር ለኢትዮጵያ አስፈላጊ አገራት ናቸው የሚሉት አምባሳደር ቶፊቅ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ከነዚህ አገራት እና ተቋማት ጋር ማጠናከር ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከተባበሩት አረብ ኢምሬት (ዩኤኢ)፣ ጆርዳን እና ኳታር ውጪ ወደ ሌሎች የአካባቢው አገራት ሰራተኞችን እየላከች አይደለም፡፡