የግብጽ እና ሱዳን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ተጠናቀቀ
“የደቡብ ጠባቂው - 2” የሚል ስያሜን የተሰጠው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የሀገራቱን ድንበር ደህንነት የማስጠበቅ አላማ አለው ተብሏል
ሀገራቱ በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት የሚያደርጉት ወታደራዊ ልምምድ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ግብጽ እና ሱዳን ለቀናት ሲያደርጉት የቆዩት ወታደራዊ ልምምድ ተጠናቀቀ።
የግብጽ ጦር ቃልአቀባይ ኮሎኔል ጋሪብ አብደል ሃፊዝ እንዳስታወቁት፥ በወታደራዊ ልምምዱ ላይ የግብጽ የድንበር ጠባቂ ሃይል እና የሱዳን ወታደሮች ተሳትፈዋል።
“የደቡብ ጠባቂው - 2” የሚል ስያሜን የተሰጠው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የሀገራቱን ድንበር ደህንነት የማስጠበቅ አላማ አለው ተብሏል።
ተሳታፊዎቹ የጋራ የደህንነት ስጋቶችን በጋራ በብቃትና በፍጥነት የሚመክቱበትን ክህሎት ማዳበራቸውን ደግሞ የግብጽ የድንበር ጠባቂ ሃይል አዛዡ ሜጀር ጄኔራል ኢማድ ያማኒ ተናግረዋል።
ሀገራቱ ዘመኑ ያፈራቸውን የጦር መሳሪያዎች ተጠቅመው ፈጣን እርምጃን የሚሹ የጸጥታ ችግሮችን የሚፈቱባቸው መንገዶችም የወታደራዊ ልምምዱ አካል ነበሩ ተብሏል።
አጠቃላይ ልምምዱ የድንበር ላይ ድህንነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው ይባል እንጂ ዝርዝር የልምምዱ መልክ በግብጽ ጦር መግለጫ አልተጠቀሰም።
የሱዳን ጦርም ስለጋራ ወታደራዊ ልምምዱ ያለው ነገር የለም።
ሀገራቱ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረች ወዲህ ተደጋጋሚ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን እያደረጉ ነው።
ባለፈው አመት በኮርዶፋን ግዛት የተደረገውም ሆነ በግብጽ የተካሄዱ የጦር ልምምዶች ዋነኛ አላማ የሀገራቱን ወታደራዊ ትብብር ማሳደግ መሆኑ ቢነገርም ለኢትዮጵያ የሚሰዱት መልዕክትም የታሰበበት ይመስላል።
ለሳምንት የዘለቀው የሰሞኑ ልምምድም ባለፉት ሁለት አመታት እንደተካሄዱት ወታደራዊ ልምምዶች አይነት አንድምታ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
የሰሞኑ ወታደራዊ ልምምድ በተጀመረ ማግስት የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ከግብጽና ሱዳን ጋር ህጋዊ ስምምነትን ትፍራረም ዘንድ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።