ግብጽ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከአምስት ሀገራት ጋር ምክክር ጀመረች
በምክክር መድረኩ ላይ ግብጽን ጨምሮ ባህሬን፣ አረብ ኢምሬትስ፣ ኢራቅ እና ጆርዳን በመሳተፍ ላይ ናቸው ተብሏል
ፕሬዝዳንት አልሲሲ የሚመሩት ይህ መድረክ ኒው አላሜን በተሰኘችው የወደብ ከተማ እየተካሄደ ነው
ግብጽ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ከአምስት የአረብ ሀገራት ጋር ምክክር ጀመረች፡፡
የግብጹ ፕሬዝዳንት ያዘጋጁት የአረብ ጉባኤ በሜድትራኒያኗ የወደብ ከተማ ኒው አላሜን ከተማ በመካሄድ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ግብጽን ጨምሮ ባህሬን፣ ኢራቅ፣ አረብ ኢምሬት እና ጆርዳን የተሳተፉ ሲሆን የጉባኤው አጀንዳ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋነኛው እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
መሪዎቹ በዚህ ጉባኤ ላይ ከህዳሴው ግድብ በተጨማሪም በየመን፣ ሶሪያ እና ሊቢያ ስላሉ ግጭቶች ጉዳዮች እንደሚወያይም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የእስራኤል ጋዛ ጦርነት፣ ሌላኛው የጉባኤው አጀንዳ እንደሚሆን የተጠቀሰ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ሌሎች የአረብ ሊግ አባል ሀገራት ስለመሳተፋቸው አልተጠቀሰም፡፡
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል ዩኒት 9 የሚባለው ሁለተኛው ተርባይን የተሳካ ተከላ እና ሙከራ ከተደረገ በኋላ ኃይል የማመንጨት ስራው ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ይህ የግድቡ ሁለተኛው ዩኒት 270 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በምረቃው ወቅት ገልጸዋል።
ባሳለፍነው የካቲት ወር 2014 ዓ.ም ግድቡ ካሉት ተርባይኖች ውስጥ አንዱ የሆነው እና ዩኒት 10 የሚል መጠሪያ ያለው ተርባይን 270 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም ታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ 540 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማብሰሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር በሶስተኛው ዙር ውሃ ሙሌት 22 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ገደማ ውሃ መያዝ የሚያስችል እና ሁለት ተርባይኖችን ማንቀሳቀስ የሚያስችል ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል
“ሆኖም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራተ ላይ የውሃ እጥረት እንዳያጋጥም ኢነርጂ እያመነጨን በታቸኛው ውሃ ማስተንፈሻ (ቦተም አውት ሌት) በኩል ውኃ በከፍተኛ ሁኔታ አንድም ቀን ሳይቋረጥ እንዲሄድ እየተደረገ ነው” ሲሉ አክለዋል።
“የሚፈሰውን ውሃ ብንይዝ ኖሮ በአጠረ ጊዜ ውስጥ ውሃ መሙላት ይቻል ነበረ ነገር ግን የኛ ፍላጎት የመልማት ብ መሆኑን ለማሳየት ውሃ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እየለቀቀች ነው” ም ብለዋል።
ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ በግድቡ አስተዳደር ጉዳይ ዙሪያ የሶስትዮች ንግግር እና ድርድር ከመጀሩ ዓመታት ቢያስቆጥሩም እስካሁን ወደ ስምምነት አልመጡም፡፡