ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት በተያዘው ጊዜ አከናውናለሁ ማለቷን ግብፅና ሱዳን ተቃወሙ
ሱዳን 2ኛ አማራጭ መጀመሯ እና አሜሪካ ከሦስቱም ሀገራት ጥያቄ ካልቀረበላት ጣልቃ እንደማትገባ መገለጹ ይታወሳል
ግብፅ “ይህ የተናጥል ውሳኔ የቀጣናውን ደህንነት እና መረጋጋት የሚጎዳ ነው" ብላለች
ኢትዮጵያ በሚቀጥለው ክረምት ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከማከናወን የሚያግዳት ምንም ምክንያት እንደሌለ እና በተያዘው ጊዜ ሙሌቱን እንደምትጀምር የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚሁ ጉዳይ ባወጣው መግለጫ ፣ ኢትዮጵያ ያለስምምነት የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት ለማከናወን መወሰኗን ግብፅ እንደምትቃወም አስታውቋል፡፡ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አሕመድ ሀፊዝ “የኢትዮጵያ መግለጫ ሁለቱን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የማጥቃት ፍላጎቷ ዳግም የታየበት እንዲሁም በግብፅ እና በሱዳን ህዝቦች ላይ ስጋት የሚያሳድር በመሆኑ ግብፅ ትቃወማለች" ብለዋል፡፡
አክለውም “ይህ የተናጥል ውሳኔ የቀጣናውን ደህንነት እና መረጋጋት የሚጎዳ ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተሰጠው መግለጫ “ለሕዳሴ ግድብ ችግር መፍትሄ ለማምጣት ድርድር ለማድረግ በኢትዮጵያ በኩል የፖለቲካ ፍላጎት አለመኖሩን የሚያንፀባርቅ ነው” ያሉም ሲሆን አራት ዓለም አቀፍ አካላት የማደራደር ስራውን በማከናወን አፋጣኝ እልባት እንዲያመጡም ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያን አቋም እንደምትቃወም የገለጸችው ሌላኛዋ የተፋሰሱ ሀገር ሱዳን ፣ ከዚህ ቀደም እንደምትለው የግድቡ ያለስምምነት መሞላት 29 ሚሊዮን ዜጎቿን እንደሚጎዳ አንስታለች፡፡
በግድቡ ድርድር የሱዳን የቴክኒክ ቡድን ኃላፊ ሙስጠፋ ሁሴን በሰጡት መግለጫ ሱዳን በአደራዳሪነት ከጋበዘቻቸው አራት አካላት አዎንታዊ ምላሽ በማግኘት ላይ ናት ብለዋል፡፡ ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ በሱዳን የተጋበዙት አሜሪካ ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ተመድ ሰምምነት ላይ ለመድረስ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸውም ነው የጠቀሱት፡፡
በኢትዮጵያ በኩል የተሰጠው መግለጫ ሀገሪቱ ከያዘችው አቋም መቀጠሏን ያሳያል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ለብዙ ጊዜ የቆዩት እና አረብኛ አቀላጥፈው የሚናገሩት የአሜሪካ ቀጣናዊ ጉዳዮች ቃል አቀባይ ሳሙኤል ወርበርግ ፣ “ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ይፋዊ ግብዣ ካልቀረበላት ዋሺንግተን በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ጣልቃ የምትገባበት አግባብ የለም” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ “አሜሪካ የሕዳሴ ግድብ ድርድር መፍትሄ የሚያገኘው በሶስቱ ሃገራት መካከል በሚደረግ ንግግር ነው ብላ ታምናለች” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ታዋቂው ሱዳናዊ የፖለቲካ ተንታኝ ኦስማን ማርጋኒትናንት ከስካይ ኒውስ አረብኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፣ ተመድ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካና የአፍሪካ ሕብረት በአደራዳሪነት ይግቡ የሚለውን ሀሳብ ኢትዮጵያ ውድቅ ካደረገች በኋላ ሱዳን አዲስ የዲፕሎማሲ ዘዴን ትጠቀም ይሆን? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “እኔ አይመስለኝም” ብለዋል፡፡ ለዚህም ምክንያት “ካርቱም የጥንቃቄ እርምጃዎችን ጀምራለች” የሚል ነው፡፡ የድርድሩ ጉዳይ እንደማያዛልቃት የተረዳችው ሱዳን አሁን ላይ ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ “ወደ ሁለተኛ አማራጭ እየተሸጋገረች ነው” ሲሉም ተናግረዋል።