“ግብፅና ሱዳን የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርነትን ኮንጎ እስክትረከብ ድርድሩ እንዲዘገይ ይፈልጋሉ” አምባ. ዲና
ካርቱምና ካይሮ የግድቡ ጉዳይ ወደ ተመድ እንዲሄድ ይፈልጋሉም ተብሏል
ሁለቱ ሀገራት ለሕዳሴ ግድብ ድርድር ከደቡብ አፍሪካ ይልቅ ኮንጎን ለምን መረጡ?
ግብፅና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ድርድር ከአንድ ወር በኋላ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የምትሆነው ዲሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኮንጎ ኃላፊነቱን እስክትረከብ እንዲዘገይ ፍላጎት እንዳላቸው ኢትዮጵያ አስታወቀች፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንዳሉት ካይሮና ካርቱም የግድቡ ድርድር ቶሎ እንዳይጠናቀቅ እና አሰልቺ እንዲሆን እያደረጉ ነው፡፡
ሀገራቱ የደቡብ አፍሪካ የሊቀ መንበርነት ጊዜ እስኪያበቃ ድርድሩ እንዲዘገይ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት ቃል አቀባዩ “ካርቱምና ካይሮ ድርድሩን አሰልቺ አንዲሆንም አድርገዋል” ነው ያሉት፡፡
ሀገራቱ የሕዳሴ ግድብ ድርድር “በጥቅሉ በአፍሪካ ሕብረት ፣ በተናጠል ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ሊቀመንበርነት መፍትሄ እንዲያገኝ ፍላጎታቸው አይደለም” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የወቅቱ የሕብረቱ ሊቀ መንበር ደቡብ አፍሪካ ለድርድሩ እልባት ሳትሰጥ የሊቀመንበር ጊዜዋ እንዲጠናቀቅ የሚፈልጉት ሁለቱ ሀገራት ፣ የሕዳሴ ግድብ ድርድር መሪነት ወደ ዲ.አር. ኮንጎ እንዲሸጋገር እንደሚፈልጉ ነው አምባሳደር ዲና ያስታወቁት፡፡
የግድቡ ድርድር ከአሜሪካና የዓለም ባንክ አደራዳሪነት ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲመለስ የማድረጉ ሥራ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ግብፅ ለምን ድርድሩ በኮንጎ መሪነት እንዲቀጥል ሻተች?
ከአውሮፓውያኑ የካቲት 2021 ጀምሮ ለአንድ ዓመት ያህል ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ትሆናለች፡፡ ኪንሻሳ ይህንን ኃላፊነት ለመረከብ አንድ ወር ብቻ ነው የሚቀራት፡፡ ከዚህ ቀደም የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ በኪንሻሳ ተገኝተው ፣ ከፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ የተላከ መልዕክትን ለኮንጎ ፕሬዚዳንት ፍሊክስ ቺሲኬዲ ማድረሳቸውን አህራም መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተላው ደብዳቤ ትኩረት ያደረገው ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታና የድርድር ሂደት ላይ እንደሆነም ነው በወቅቱ የተዘገበው፡፡
ፕሬዚዳንት ፍሊክስ ቺሲኬዲ በምላሹ ለግብፁ አቻቸው በአማካሪያቸው በኩል በላኩት መልዕክት በሕዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ሀገራቸው ከግብጽ ጎን እንደምትቆም ማረጋገጣቸውን የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ ሀገራቱ በጋራ የሚያከናውኗቸው የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ከመኖራቸውም በተጨማሪ ግብፅ ለኮንጎ የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ እንደነበረም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እናም ሁለቱ ሀገራት ካላቸው ቅርርብ የተነሳ ፣ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚደረገው ድርደር ከደቡብ አፍሪካ ወደ ኮንጎ የመዛወሩን ጉዳይ ግብፅ አጥብቃ ትፈልገዋለች ነው የተባለው፡፡
በዚህም ምክንያት ነው ድርድሩ እልባት ሳያገኝ ደቡብ አፍሪካ የሊቀመንበርነቷ ጊዜዋ እንዲያልቅ ግብፅና ሱዳን ሰበቦችን በመደርደር ጊዜ መግዛት የሚፈልጉት ተብሏል፡፡ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ11 የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት አንዷ ነች፡፡
የሰሞኑ ድርድር ከምን ደረሰ?
ሀገራቱ ድርድሩ እንዲዘገይ ከመፈለጋቸውም በተጨማሪ ጉዳዩ ወደ ተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት እንዲሄድ ፍላጎት እንዳላቸው ነው ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ያነሱት፡፡
የሕዳሴ ድርድር ከ10 ቀናት በፊት መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን አደራዳሪው የአፍሪካ ሕብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ያቀረበው የአደራዳሪነት ሀሳብን ግብፆች ሳይቀበሉት ቀርተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
የሦስቱም ሀገሮች ባለሙያዎች እስካሁን የነበሩትን አንድነቶችና ልዩነቶች ለይተው ለሚኒስትሮች የጋራ ስብሰባ እንዲያቀርቡ የቀረበውን ሀሳብ ደግሞ ሱዳኖች ሳትቀበል ቀርታ ነበር፡፡
ካርቱም ለዚህ ያቀረበችው ምክያትና ሰበብ ከአፍሪካ የባለሙያዎች ቡድን ጋር በግል መደራደር ያስፈልጋል የሚል እንደነበር አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡ የሚኒስትሮች ስብሰባ ሲደረግ አደራዳሪው ወገን ሱዳንን ከባለሙያዎቹ ጋር መነጋገር እንደምትችል ቢገልጽላትም እንደገና ቢጋር ካልቀረበና (የባለሙያዎች ቢጋር) በአፍሪካ ሕብረት ካልጸደቀ አንደራደርም በሚል ከድርድሩ መውጣቷ ተገልጿል፡፡
ይህም ለድርድሩ አስተባባሪ በሪፖርት መልክ መቅረቡን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ሱዳን ወደ ድርድሩ መመለሷን በትናንትናው ዕለት አስታውቃለች፡፡
“በሰበብ ባስባቡ የሚወጡት ሱዳንና ግብፅ ናቸው” ያሉት አምባሳደር ዲና ፣ በኢትዮጵያ በኩል የሦስትዮሽ ድርድሩ ስኬታማ እንዲሆንና ድርድሩን የማስቀጠል ፍላጎት እንዳለ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡