ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የድንበር ውዝግብ በሰላም እንድትፈታ ደቡብ ሱዳን ጠየቀች
ፕሬዚዳንት ኪር ሀገራቱ ለድንበር ችግር ዲፕሎማሲን ብቻ እንዲመርጡ ጠይቀዋል
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የድንበር ውዝግብ በሰላም መፍታት እንዳለባት የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ጠየቁ
ፕሬዚዳንት ኪር የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት አባል የሆኑትን ቼምስ አል ዲን ካባሽ እና ተጠባባቂ የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦመር ጋማር ኢልዲንን በጁባ አነጋግረዋል፡፡ ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮ ሱዳን ድንበር ከሰሞኑ የተፈጠረውን ሁኔታ ለፕሬዚዳንት ኪር ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኪር ካርቱምና አዲስ አበባ የድንበር እሰጥ አገባውን በድርድርና በሰላማዊ መንገድ ብቻ መፍታት እንዳለባቸው ጁባ ለተገኙት የሱዳን ባለሥልጣናት መግለጻቸውን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን የሚጋሩትን ድንበር በተመለከተ በዲፕማሲያዊ መንገድ ብቻ መፍታት ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንት ኪር በቀጠናው ከዚህ በኋላ ጦርነት መኖር እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡
ሱዳን ባለፈው ኅዳር ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ ወታደሮችን ማስጠጋቷና የኢትዮጵያን ሚሊሻዎችና አርሶ አደሮችን ማፈናቀሏ የተዘገበ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ልዑክም ይህንኑ ጉዳይ ካርቱም ተገኝቶ መገለጹ ይታወሳል፡፡
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የኤርትራና ግብጽ ባለሥልጣናት ከሱዳን ሹሞች ጋር በካርቱም ውይይት አድርገዋል፡፡
ከ15 ቀናት በፊት የኢትዮጵያ እና የሱዳን ድንበር የጋራ ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴ በካርቱም ያደረገው ውይይት ያለስምምነት መጠናቀቁን የሱዳን የሽግግር መንግስት ምንጮች በወቅቱ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ውይይቱ የተመራው በኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና በሱዳን ካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አምባሳደር ኦማር በሽር ማኒስ ነበር፡፡
ሱዳን በድንበር አካባቢ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንድታቆም ኢትዮጵያ ማሳሰቧ የሚታወስ ሲሆን በድንበር ላይ ያለው ችግር በውይይትና በንግግር እንዲፈታም በተደጋጋሚ ጠይቃለች፡፡
የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር የጋራ ከፍተኛ የፖለቲካ ኮሚቴው ውይይቱ በሌላ ጊዜ ለማድረግ ተለዋጭ ቀጠሮ ተይዟል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ ከሱዳንጋር ያላትን ግንኙነት እንደምትንከባከብ ገልጸው በድንበር ላይ የተፈጠረው ችግር ግን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ እንዲፈታ ትፈልጋለች ብለዋል፡፡
በአውሮፓውያኑ 2014 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የወቅቱ ሱዳን መሪ ኦማር ሐሰን አልበሽር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ድንበሩ መሬት ላይ የሚመላከትበትን የመጨረሻ ቀን እንዲያሳውቁ መመርያ አስተላልፈውላቸው እንደነበር ይታወሳል።