ሱዳን ወደ ሕዳሴው ግድብ ድርድር መመለሷን ገለጸች
ሀገሪቱ ትናንት ውድቅ ያደረገችውን ፣ ከባለሙያዎች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ የማድረግ ሀሳብ መቀበሏን ገልጻለች
“ግድቡን በተመለከተ ሌሎች አማራጮች ይኖራሉ” ሲሉ የሱዳን ዉጭ ጉ/ሚኒስትር ተናግረዋል
የአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች በሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ከፍተኛ ሚና ካልኖራቸው በድርድሩ አልሳተፍም በሚል ሱዳን ራሷን ከድርድሩ ማግለሏን ገልጻ ነበር፡፡ በትናንትናው ዕለት በደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ሕብረት አስፈጻሚ ም/ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት ፣ የኢትዮጵያ ፣ ግብፅ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ሚኒስትሮች የሕዳሴው ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት እንዲካሄድ ስምምነት ተደርሶበት የነበረው ስብሰባ ሱዳን ባለመገኘቷ ምክንያት ሳይካሄድ መቅረቱም የሚታወቅ ነው፡፡ በትናንትናው ምክክርም የአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲሰጣቸው እና ስብሰባው ከባለሙያዎች ጋር ብቻ እንዲደረግ የሚል አቋም በመያዝ ይህ ካልሆነ በድርድሩ አልሳተፍም ብላ ሱዳን ራሷን አግልላለች፡፡
የሱዳን ሉዓላዊነ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄኔራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን ፣ የመስኖ እና የውሃ ሀብት ሚኒስትሩን ፕሮፌሰር ያሲር አባስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦማር ቀመረዲን ዛሬ ሰኞ ጥር 03 ቀን 2013 ዓ.ም በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ካነጋገሩ በኋላ ታዲያ ሀገሪቱ አቋሟን ቀይራለች፡፡ ሦስቱ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገውን ድርድር አስመልክቶ የእስካሁን ክንውኖችን እና በቅርቡ ድርድሩ በተቋረጠበት ምክንያት ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
ፕሮፌሰር አባስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሱዳን አቋም ሕብረቱ በመረጣቸው ባለሙያዎች አማካይነት ለአፍሪካ ሕብረት የአመቻችነት ሚና የመስጠት አስፈላጊነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልፀው ባለፈው ጊዜ የተካሄደው ድርድር ምንም ፋይዳ እንዳልነበረው አንስተዋል፡፡
የመስኖና የውሃ ሀብት ሚኒስትሩ በባለሙያዎቹ የተዘጋጀውን የመጀመሪያ ረቂቅ ስምምነት ሱዳን መቀበሏን አረጋግጠው በሚቀጥለው እርምጃ ላይ ግልፅ ነገር እንዲኖር መጠየቋንም ተናግረዋል፡፡ ሀገራቱ በረቂቅ ስምምነቱ ላይ ከአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ጋር በሚያደርጉት የሁለትዮሽ ስብሰባዎች አስተያየታቸውን እንደሚገልጹ እና ረቂቁን እንደሚያዘጋጁም ጠቁመዋል፡፡ ይህ ሀሳብ በትናንትናው ምክክር ሱዳን አልቀበልም ያለችው ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ያለ ስምምነት የሁለተኛ ዓመት የውሃ ሙሌት ለመቀጠል እቅድ መያዟን ሱዳን በጽኑ እንደምትቃወም ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ሕብረት ሱዳን ማሳወቋን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ይህ "ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ እንዲሁም በሱዳን የሮሳሪስ ግድብ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም" ማሳወቃቸውን ነው ሚኒስትሩ አባስ የገለጹት፡፡
ፕሮፌሰር አባስ ድርድር ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት ከሁሉ የተሻለ መፍትሄ እንደሆነ ያላቸውን እምነትም ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኦማር ቀመረዲን በበኩላቸው ሱዳን "ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች" በሚለው መርህ መሰረት የአፍሪካ ሕብረት ባለሙያዎች ከቀድሞው የላቀ ሚና እንደሚኖራቸው በመተማመን ወደ ሕዳሴ ግድብ ድርድር መመለሷን አመልክተዋል፡፡
ደቡብ አፍሪካ የሕብረቱ ሊቀመንበር እንደመሆኗ ልትጫወት የምትችለውን ሚና በተመለከተ ሱዳን ለሀገሪቱ ሀሳብ ማቅረቧንም ቀመረዲን ገልጸዋል፡፡ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በሚቀጥለው የካቲት ላይ በአፍሪካ ሕብረት ሰብሳቢነት በሚደረገው አዲስ ውይይት፣ የሱዳንን ፍላጎት ለማሳካት ሀገሪቱ የተለያዩ ተግባራትን እንደምታከናውንም ተናግረው ፣ “ይህ ካልተሳካ ጉዳዩን በተመለከተ ሌሎች አማራጮች ይኖራሉ”ም ብለዋል፡፡ አማራጮቹ ምን እንደሆኑ ግን ሚኒስትሩ የገለጹት ነገር የለም፡፡