በዩክሬኑ ትርምስ ኢኮኖሚዋ የተጎዳው ግብጽ የአይ.ኤም.ኤፍን ድጋፍ እየተማጸነች ነው
ግብጽ አይኤምኤፍ ድጋፍ የምትሻው ሁለገብ የኢኮኖሚ መርሃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ ነው ተብሏል
ግብጽ ከሩሰያ እና ዩክሬን ስንዴን በመሸመት በዓለም አንደኛ መሆኗ ይታወቃል
በዩክሬኑ ትርምስ ኢኮኖሚዋ ኩፉኛ የተጎዳው ግብጽ የዓለም አቀፉን የገንዘብ ድርጅት/አይ.ኤም.ኤፍ/ ድጋፍ እየተማጸነች ነው ተባለ፡፡
ስንዴን በመሸመት በዓለም አንደኛ እንደሆነች የሚነገርላት ግብጽ፤ የእህል ምርቶች ግዢ የምትፈጽምባቸው ዋናዎቹ ሀገራት በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬን በመሆናቸው ጦርነቱ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደፈጠረ ይገለጻል፡፡
በዚህም ግብጽ በተለያዩ ሀገራት ያጋጠመው የዋጋ ንረት ለመቆጣጠርና ሁለገብ የኢኮኖሚ መርሃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ በሚል የአይ.ኤም.ኤፍ ድጋፍ ጠይቃለች፡፡
የግብጽ መንግስት ድጎማ በማድረግ ለህዝብ በሚያቀርበውን ዳቦ ሳይቀር ያለተጋነነ ዋጋ ለመተመን የሚያስችል ህግ ይፋ ማድረጉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የግብጽ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የቱሪዝሙ ዘርፍም ቢሆን፤ የነበረው የኮሮና ወረርሺኝ እንደሁም ካለው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ጋር ተዳምሮ በከፍተኛ ሁኔታ መዳከሙ እየተገለጸ ነው፡፡
በግብጽ የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ለማረጋጋት መንግስት ለመብራት አገልግሎት ሲከፈል የነበረው ዋጋ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ ማድረጉ ይፋ ያደረገው በዚህ ሳምንት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት /አይኤምኤፍ/ የግብጽ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች እንደሚያደንቅ መግለጹም እንዲሁ የሚታወስ ነው፡፡
ከተጀመረ አንድ ወር ያስቆጠረው ሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በበርካታ ሀገራት የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት እስከመሆነ የደረሰ አሳሳቢ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አጀንዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡