የሱዳን ተቃዋሚዎች ሃገሪቱን ከግብጽ የሚያገናኘውን መንገድ ዘጉ
ካርቱምን ከፖርት ሱዳን የሚያገናኝ ነው የተባለለት መንገዱ በሰሜን በኩል ግብጽን ከሱዳን የሚያስተሳስር ነው
ተቃዋሚዎቹ መንገዱን የዘጉት የሱዳን ጦር ስልጣን እንዲያስረክብ ለማስገደድ ነው መሆኑን ገልጸዋል
የሱዳን ተቃዋሚዎች ሃገሪቱን ከግብጽ የሚያገናኘውን መንገድ ዘጉ፡፡
የሱዳን ጦር ከሶስት ወራት በፊት ባካሄደው መፈንቅለ መንግስት ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ ሱዳናዊያን ተቃውሟቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
ተቃዋሚዎቹ ሱዳንን ከግብጽ የሚያገናኘውን ሸሪያን አል ሺማል የተሰኘውን ዋና መንገድ መዝጋታቸው ተገልጿል፡፡
ተቃዋሚዎቹ መንገዱን የዘጉት በጀነራል አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር እንዲያስረክብ ለማስገደድ መሆኑን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል፡፡
በቀድሞው የሱዳን ፕሬዘዳንት የስልጣን ጊዜ ተቃውሞዎችን በማስተባበር የሚታወቁ አንድ ተቃዋሚ እንዳሉት “ከሱዳን ወደ ግብጽ በዚህ መንገድ የሚሄድ የውጪ ንግድ እንቅስቃሴዎችን ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ እናደርጋለን“ ብለዋል፡፡
በተቃዋሚዎች የተዘጋው መንገድ ካርቱምን ከፖርት ሱዳን የሚያገናኘው እና በሰሜን በኩል ግብጽን የሚያስተሳስረውን እንደሚጨምርም ተገልጿል፡፡
በሱዳን አሁንም በወታደራዊ አስተዳድሩ ላይ ተቃውሞዎች የቀጠሉ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን ተመድን ጨምሮ አውሮፓ እና አሜሪካ ወታደራዊ አመራሩ ለሲቪል አስተዳድር ስልጣን እንዲያስረክብ በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡
በዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የሚመራው የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ኢጋድ ከሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመምከር ካርቱም ይገኛሉ፡፡