ፖለቲካ
ግብጽ ዓረብ ሊግ በዩክሬን ጉዳይ ተቀምጦ እንዲመክር አስቸኳይ ስብሰባ ጠራች
የዓረቡ ዓለም ሀገራት በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ዙርያ የተለያየ አቋም ሲያራምዱ ተስተውለዋል
በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እስካሁን 64 ሲቪሎች ሲሞቱ 174 መቁሰለቸው ተመድ ገልጿል
ግብጽ የዓረብ ሊግ በዩክሬን ጉዳይ ተቀምጦ እንዲመክር አስቸኳይ ስብሰባ ጠራች፡፡
ግብጽ የጠራቸው ስብሰባ በሊጉ አባል ሀገራት ተወካዮች አማካኝነት የሚካሄድ ሲሆን በወቅታዊ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ዙርያ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ የዓረቡ ዓለም ሀገራት በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ዙርያ የተለያየ አቋም ሲያንጸባርቁ ተስተውለዋል፡፡
ሶርያ የሩሲያን ወታደራዊ ዘማቻ ስትደግፍ ልባኖስ ድርጊቱን ኮንናለች፣ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ አቋም ለመያዝ እንደምትቸገር አስታውቃለች፡፡
በሌላ በኩል ግብጽ ጉዳዩ እጅጉን እንደሚያሳስባትና በዩክሬን የተፈጠረው ትርምስ በአጭሩ መቋጫ ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳለት ገልጻለች፡፡
ሰሜን አፍሪካቷ ግብጽ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ጥቃት መሰንዘር መጀመሯን ተከትሎ በግብጽ የነበሩ ዩክሬናውያን ቱሪስቶች ሁኔታዎች እስኪረጋጉ በሀገሪቱ ያላቸውን ቆይታ ማራዘም ይችላሉ ስትልም ፈቃድ ሰጥታለች፡፡
የተመድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እስካሁን 64 ሲቪሎች ሲሞቱ 174 ቆስለዋል፡፡
ግብጽ የወቅቱ የአረብ ሊግ ሊቀመንበር ሆና መመረጧ ይታወሳል፡፡