የጅቡቲና ግብጽ መሪዎች በሕዳሴ ግድብና በቀይ ባህር ላይ ያተኮረ ውይይት አደረጉ
የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማርጊሌ የአዲስ አበባ ቆይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላዳ ካይሮ አቅንተዋል
መሪዎቹ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ላይም ንግግር አድርገዋል ተብሏል
የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እና ግብፁ አቻቸው ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው የሕዳሴ ግድብ ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረጋውን አስታወቁ።
መሪዎ ቹ ከሕዳሴ ግድብ ባለፈም በቀይ ባህር ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል።
ለ35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ አዲስ አበባ የሰነበቱት የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ካይሮ ከገቡ በኋላ ነው ውይይት ማድረጋቸው የተገለጸው።
ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦመር ጊሌ ካይሮ ከገቡ በኋላ ከግብፁ አቻቸው ጋር የቀይ ባህርን ደህንነት የተመለከተ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ እና እስማኤል ኦማር ጊሌ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ሁኔታ እና የቀይ ባህርን ደህንነት አንስተው መነጋገራቸው ተገልጿል።
የቀይ ባህር ደህንነት ለግብፅ እና ጅቡቲ የመሪዎች ጉባኤ ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ እንደሆነም ከካይሮ የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።
የግብፁ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ በቤተ መንግስት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ሁኔታ እና የቀይ ባህር ደህንነት ውይይት እንደተደረገበት ገልጸዋል።
መሪዎቹ የአፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን መሥራትን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተነግሯል።
በግብፅ እና በጅቡቲ መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም መክረዋል ነው የተባለው።
አብዱል ፈታህ አልሲሲ በመግለጫቸው የሕዳሴ ግድብን የተመለከተ ሃሳብም ሰጥተዋል ተብሏል፡፡ በመግለጫቸውም ካይሮ አሁንም በሕዳሴ ላይ አስገዳጅ ስምምነት እንደምትፈልግ አንስተዋል።
የጅቡቱውፕሬዝዳንት ከግብፁ አቻቸው ጋር ስላደረጉት ውይይት እስካሁን የሰጡት መረጃ የለም።
ሱዳን እና ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ያደረጉት ስምምነት ካለውጤት መቆሙን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ሀገራቸው ግን አሳሪ ስምምነት እንዲኖር ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል ሲሉ የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
አዲስ አበባ፣ ካይሮ እና ካርቱም የሕዳሴ ግድብ ድርድርን በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን ድርድሩ አሁን ላይ ቆሟል።