የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለመጀመሪያ ጊዜ ሶሪያ ገብተዋል
ሚኒስትሩ ሳሜህ ሹክሪ በርዕደ መሬት ለተጎዳችው ደማስቆ "የወንድማማችነት" መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሏል
ሶሪያ በ2011 የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች ወዲህ የአል አሳድ አስተዳደር ከአረብ ሀገራት ድጋፍ ማጣቱ ይታወቃል
የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ለይፋዊ ጉብኝት ሶሪያ ገብተዋል።
የግብፅ ከፍተኛ ባለስልጣን ከፈረንጆቹ 2011 ወዲህ ደማስቆ ሲገባም የሹክሪ የመጀመሪያ ነው ተብሏል።
የሚኒስትሩ ጉብኝት የፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ አስተዳደር ከአረብ ሀገራት ጋር ግንኙነቱን ማደስ መጀመሩን እንደሚያሳይም ተገልጿል።
ሳሜህ ሹክሪ ዛሬ ደማስቆ ሲደርሱ የሶሪያ አቻቸው ፈይሰል ማክዳድ አቀባበል ተደርጎላቸዋል ብሏል የሶሪያው ብሄራዊ የዜና ወኪል ሳና።
ሶሪያ ከሶስት ሳምንት በፊት ከባድ ርዕደ መሬት ስታስተናግድ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ ለፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ስልክ መደወላቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ሹክሪ በደማስቆ በሚኖራቸው ቆይታም የሀገራቱን ወዳጅነት የሚያጠናክር ውይይት እንደሚያደርጉ ነው የተገለፀው።
ከርዕደ መሬት አደጋው በኋላ የሶሪያን ተቃዋሚዎች ታስታጥቅ የነበረችው ዬርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በደማስቆ ጉብኝት ማድረጋቸውም አይዘነጋም።
ከአረብ ሊግ አባልነት የታገደችውን ሶሪያ የቀጠናው ሀገራት ፊታቸውን አዙረውባት ቢቆዩም በተለይ ከሶስት ሳምንት በፊት ከደረሰው ርዕደ መሬት በኋላ ግንኙነታቸውን ማደስ ጀምረዋል።
ከአመታት በፊት የሻከረውን ግንኙነት ማለዘብ የጀመረችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስም የሰብአዊ ድጋፎችን ለሶሪያውያን እየላከች ነው።
የአሜሪካ መንግስት ግን የአረብ ሀገራቱን ከአሳድ መንግስት ጋር ዳግም መቀራረብ በበጎው አይመለከተውም።
12 አመቱን በያዘው ጦርነት የአሳድ መንግስት ያሳየውን ጭካኔ በመጥቀስም አፋጣኝ ፓለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ይጠይቃል።
የአረብ ሀገራቱ ግን ስድስት ሺህ ገደማ ሰዎችን ገድሎ ሚሊየኖችን ላፈናቀለው አደጋ ምላሽ መስጠት ይቅደም ብለዋል።
የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪም የሶሪያ ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ቱርክ ያቀናሉ ተብሏል።
በፈረንጆቹ 2013 በአብዱልፈታህ ኤልሲሲ ከስልጣናቸው በሃይል የተነሱት ሙሀመድ ሙርሲ ከቱርክ ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንደነበራቸው ይነገራል።
የኤልሲሲ የመንግስት ግልበጣም የካይሮና አንካራን ግንኙነት እንዲሻክር ማድረጉን ሬውተርስ አስታውሷል።
ይህን ግንኙነት ለማደስም ሹክሪ ዛሬ አንካራ እንደሚገቡ ይጠበቃል።