ግብፅ 38 ሰዎች በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ወሰነች
በ2019 የተቀሰቀሰውን አመጽ በማቀጣጣልና በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ሰዎች ናቸው ውሳኔው የተላለፈባቸው
በተመሳሳይ ወንጀል የተከሰሱ ህጻናትን ጨምሮ 44 ሰዎች ደግሞ ከ5 እስከ 15 አመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል
የግብፅ ፍርድ ቤት ትናንት 38 ሰዎች በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
የእድሜ ልክ እስራት ከተፈረደባቸው መካከል በስፔን በስደት ላይ የሚገኙት ነጋዴ ሞሃመድ አሊ ይገኙበታል።
ሞሃመድ አሊን ጨምሮ ሌሎች በእድሜ ይፍታህ የተቀጡት በ2019 የተቀሰቀሰውን አመጽ በማቀጣጣልና በሙስና ወንጀል የተከሰሱ ናቸው።
በግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በሚወስዷቸው እርምጃዎች ምክንያት ህዝባዊ ተቃውሞዎች በብዛት አይታዩም።
በፈረንጆቹ 2019 ግን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚንቀሳቀሱ ምስሎች እና መረጃዎች ቀላል የማይባል ንቅናቄ ፈጥረው የአደባባይ ተቃውሞዎች መከሰታቸውን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
ይህንን የማህበራዊ ሚዲያዎች ዘመቻ በመምራት ረገድ ትልቅ ድርሻ የነበረው ሞሃመድ አሊ ነው።
የሽብር ወንጀሎችን የሚመለከተው የግብጽ ፍርድ ቤት ትናንት ባስቻለው ችሎትም ሞሃመድንን ጨምሮ 23 ሰዎች በሌሉበት የእድሜ ልክ እስራት ፈርዶባቸዋል።
በተመሳሳይ የአመጽ እና ሙስና ወንጀል የተከሰሱ ህጻናትን ጨምሮ 44 ሰዎችም ከ5 እስከ 15 አመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑ ተገልጿል።
ተከሳሾቹ በግብፅ የጸጥታ ተቋማትና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር በመቀስቀስ እንዲሁም በ2019 በስዊዝ ከተማ በተፈጠረው አመጽ በመሳተፍ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው።
በወቅቱ ካይሮን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ግብጻውያን በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፥ የተወሰኑት መፈታታቸውንና ቀሪዎቹ በትናንትናው እለት በእስራት መቀጣታቸውን ነው ዘገባው ያከለው።
21 መሰል ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ ግብጻውያን ከወንጀል ነጻ ተብለው መለቀቃቸውንም ኦሳማ ባዳዊ የተባሉ ጠበቃ ተናግረዋል።