በግብጽ የሚደገፈው ምስራቃዊው የሊቢያ ጦር ሽንፈትን እያስተናገደ መሆኑ ግብጽን ክፉኛ አሳስቧታል
ግብጽ ጦሯን ወደ ሊቢያ እንድታስገባ የሀገሪቱ ፓርላማ ወሰነ
የግብጽ ፓርላማ ትናንት ባደረገው ዝግ ስብሰባ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ የሀገሪቱን ጦር በሊቢያ እንዲያዘምት ወስኗል፡፡
በሊቢያ ተቀናቃኝ ሀይሎች መካከል የሚደረገው ጦርነት ተፋፍሞ በቀጠለበት ወቅት ነው ፓርላማው “አሸባሪ ታጣቂዎች” ብሎ የፈረጃቸውን ሀይሎች ለመፋለም የግብጽ ጦር ሊቢያ እንዲገባ የፈቀደው፡፡
በግብጽ፣ በሩሲያ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሚደገፈው እና በጄነራል ካሊፋ ሀፍታር የሚመራው የሊቢያ ብሔራዊ ጦር ዓለም አቀፍ እውቅና ባለው እና በቱርክ በሚደገፈው ብሔራዊ የስምምነት መንግስት ጦር ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያፈገፈገ መምጣቱ ግብጽን ክፉኛ አስጨንቋታል፡፡
ግብጽ በቀጥታ ጦሯን ለማስገባት መወሰኗ ሊቢያ የዉጭ ሀይሎች መፋለሚያ ሜዳ እንዳትሆን የሚል ስጋትን ፈጥሯል፡፡
ግብጽ በብሔራዊ ደህንነቷ ላይ አደጋ ከተጋረጠባት ሁኔታውን ቁጭ ብላ በዝምታ እንደማትመለከት ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ከመቆየታቸውም በተጨማሪ ፣ የምዕራብ ዕዝ ጦራቸው ለግዳጅ በተጠንቀቅ እንዲቆም ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡
“ሲርጥ ከታለፈ ቀይ መስመር ተጥሷል” የምትለው ግብጽ ፣ ብሔራዊ የስምምነት መንግስት ጦሩ የካሊፋ ሀፍታርን ጦር ከሲርጥ የሚያስለቅቅ ከሆነ የግብጽ ደህንነት አደጋ ዉስጥ እንደገባ ተደርጎ እንደሚታይ ትገልጻለች፡፡ ምንም እንኳን ሲርጥ ከግብጽ ድንበር 900 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ብትሆንም በግብጽ የሚደገፈው የሀፍታር ጦር ጠንካራ ይዞታ ነች፡፡
የሀፍታር ደጋፊ የሆኑ የሊቢያ ህግ አውጪ ም/ቤት አባላት ቱርክን ለመከላከል ግብጽ በሊቢያ ጦሯን እንድታስገባ በዚህ ወር ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የግብጽ ፓርላማ ትናንት ባወጣው መግለጫ ታዲያ “የግብጽ ጦር የሀገሪቱን ምዕራባዊ ድንበር ከብሔራዊ የደህንነት ስጋት ይከላከላል” ቢልም ጦሩ መቼ እንደሚዘምትም ይሁን ስለቱርክ በመግለጫው ያነሳው ነገር የለም፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትናንትናው እለት የግብጽ ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሊቢያ ጉዳይ በስልክ ዉይይት ማድረጋቸውን ኋይት ሀውስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ፕሬዝዳንቶቹ በውይይታቸው በሊቢያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እና በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር በሀገሪቱ ዉጥረት እንዳይባባስ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ማንሳታቸው ተገልጿል፡፡
ሲጂቲኤን እንደዘገበው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሊቢያ ዉጥረቶችን ማርገብ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን ጋርም ዉይይት ማድረጋቸውን ኋይት ሀውስ ይፋ አድርጓል፡፡
ሊቢያ የቀድሞ መሪዋ ሙአማር ጋዳፊ በአውሮፓውያኑ 2011 ከተገደሉበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በእርስበርስ ጦርነት ዉስጥ ትገኛለች፡፡