“የግብጽ ጦር ጠንካራ አቅም ካላቸው ሃያል የመካከለኛው ምስራቅ ጦሮች መካከል አንዱ ነው”-አል ሲሲ
ፕሬዝዳንቱ የሃገሪቱ ጦር የምዕራብ ዕዝ ማዕከልን ጎብኝተዋል
“በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ ያለን ብሄራዊ የደህንነት ፍላጎት ለማስጠበቅ የሚያስችል አቅም”ም አለው
“የግብጽ ጦር ጠንካራ አቅም ካላቸው ሃያል የመካከለኛው ምስራቅ ጦሮች መካከል አንዱ ነው”- አል ሲሲ፣ የግብጽ ፕሬዝዳንት
ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ “የግብጽ ጦር ጠንካራ አቅም ካላቸው ሃያል የመካከለኛው ምስራቅ ጦሮች መካከል አንዱ ነው” ሲሉ ተናገሩ፡፡
“ራሱን የማያስነካ ሌሎችንም የማይነካ” ሲሉ ጦሩን ያሞካሹት ባለ ፊልድ ማርሻል ማዕረጉ አል ሲሲ “በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ ያለን የግብጽን ብሄራዊ የደህንነት ፍላጎት ለማስጠበቅ የሚያስችል አቅም” እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በምዕራብ የሃገሪቱ ጦር የዕዝ ማዕከል ተገኝተው የጦሩ አየር ሃይል በምን ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገምግመዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ ለሚያስፈልግ ግዳጅ ጦሩ ዝግጁ እንዲሆን ስለማዘዛቸው አል አረቢያ የተሰኘው የሳዑዲ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል፡፡
የጦሩን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የጦር መኮንንኖችም በጉብኝት ስነ ስርዓቱ ላይ ነበሩ እንደ ፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ገለጻ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቡሊም በጉብኝቱ ወቅት ነበሩ፡፡
ምዕራብ ቀጣና ከሃገሪቱ አራት ወታደራዊ ቀጣናዎች አንዱ ሲሆን ከሊቢያ ድንበር አቅራቢያ ማርሳ ማትሩህ በተሰኘ የወደብ አካባቢ ይገኛል፡፡