ግብጽ በቀይ ባህር ንግድ መቀዛቀዝ ምክንያት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቷን ገለጸች
በእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ምክንያት የንግድ መርከቦች ስዊዝ ካናልን በመተው ሌሎች አማራጮችን እንዲከተሉ አስገድዷል
የእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ከመነሳቱ በፊት ስዊዊ ካናል በቀን 50 መርከቦችን ያስተናግድ ነበር
ግብጽ በቀይ ባህር ንግድ መቀዛቀዝ ምክንያት ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቷን ገለጸች፡፡
አንድ ዓመት ሊሆነው ሁለት ቀናት ብቻ የቀሩት የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት አሁንም የቀጠለ ሲሆን የቀይ ባህር ትራንስፖርት መስመርን ጎድቷል፡፡
በተለይም በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት የየመን ሁቲ አማጺያን ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ግንኙነት አላቸው የሚባሉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ አካባቢው ውጥረት ነግሶበታል፡፡
የግብጽ ስዊዝ ካናል ዋነኛ የቀይ ባህር ትራንስፖርት መስመር በእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ምክንያት የተጎዳ ሲሆን ግብጽ ከመስመሩ ስታገኘው የነበረው ገቢ ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱን ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ መናገራቸውን አናዶሉ ዘግቧል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ገለጻ ከሆነ ግብጽ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ከስዊዝ ካናል ስታገኘው የነበረው ገቢ በ60 በመቶ አልያም የ6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ኪሳራ አጋጥሟል ብለዋል፡፡
ግብጽ ከስዊዝ ካናል በየዓመቱ እስከ 12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ስታገኝ የቆየች ሲሆን በየቀኑ የሚመላለሱ የንግድ መርከቦች ቁጥር በ40 በመቶ እንደቀነሰም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
የግብጽ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነው የስዊዝ ካናል በፈረንጆቹ 1869 ዓመት ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት የሆነ ሲሆን ይህ የመርከቦች መጓጓዣ መስመር በቀን 50 መርከቦችን ሲያጓጉዝ ቆይቷል፡፡
ግብጽ ከአሜሪካ በገፍ ለመግዛት የተስማማችው ስቲንጀር ሚሳኤል ምንድን ነው?
በወቅቱ የግብጽ መሪ የነበሩት ካዲቭ እስማኤል ፓሻ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ይህ የመርከቦች መተላለፊያ መስመር ግንባታው 10 ዓመታትን ፈጅቷል፡፡
በዓመት 300 ሚሊዮን ቶን እቃዎች የሚተላለፉበት ስዊዝ ካናል የአገልግሎት መጠኑን ለማስፋት ግብጽ በየጊዜው የተለያዩ ማሻሻያዎችን አድርጋለች፡፡
የየመን ሁቲ አማጺያን በቀይ ባህር መርከቦች ለይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማስቆም አሜሪካ በትናንትናው ዕለት በሰነዓ እና ሆዴዳህ ወደቦች ላይ የአየር ድብደባ ፈጽማለች፡፡