የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የደህንነት ኃላፊ በኤርትራ ጉብኝት አደረጉ
ሚኒስቴሩ ግብጽ እና ኤርትራ ሶማሊያ በሁሉም ግዛቶቿ ላይ ያላትን ሉአላዊት በማስጠበቅ አስፈላጊነት ላይ ከስምምነት ደርሰዋል ብሏል
ሚኒስቴሩ አል ሲሲ ለፕሬዝደንት አፈወርቂ በላኩት መልእከት ውስጥ አንገብጋቢ የሚባሉ ጉዳዮች መነሳታቸውን ገልጿል
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ደህንነት ኃላፊ በኤርትራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ግብጽ አስታወቀች።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የግብጽ የደህንነት ኃላፊ አባስ ከማል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ባድር አብደላቲ በዛሬው እለት በአስመራ ጉብኝት በማድረግ ከኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መገናኘታቸውን አስታውቋል።
ሁለቱ የግብጽ ባለስልጣናት ከፕሬዝደንት አል ሲሲ የተላከ መልእክት ለፕሬዝደንት ኢሳያስ አድርሰዋል ብሏል መግለጫው።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው መልእክቱ "በቀጣናው ካለው የፖለቲካ እና የደህንነት ክስተት" በተጨማሪ በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያሉ ግንኙነቶችን በማሳደግ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው።
ባለስልጣናቱ በቀይ ባህር ቀጣና ሰላማዊ የማሪታይም እና አለምአቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ መኖር አስፈላጊት እና በአፍሪካ ቀንድ ስላሉት ወቅታዊ ሁኔታዎች እና ፈተናዎች ዙሪያ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ያላቸውን ሀሳብ እንዳጋሯቸው መግለጫው ጠቅሷል።
ሚኒስቴሩ አክሎም ግብጽ እና ኤርትራ በሱዳን መረጋጋት እንዲፈጠር ምክክሮችን አጠናክሮ በመቀጠል እና ሶማሊያ በሁሉም ግዛቶቿ ላይ ያላትን ሉአላዊት በማስጠበቅ አስፈላጊነት ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።
የአሁኑን የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የደህንነት ኃላፊ የአስመራ ጉብኝት ለየት የሚያደርገው ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው "የህዳሴ ግድብ" ምክንያት ካይሮ እና አዲስ አበባ በአዲስ መልክ ወዝግብ ከጀመሩ በኋላ መሆኑ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ነሐሴ ወር የግድቡ አምስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ይፋ አድርጋ ነበር። ግብጽ ይህን የኢትዮጵያ እርምጃ ተቃውማ መግለጫ ማውጣቷ ይታወሳል።
ሚኒስቴሩ አል ሲሲ ለፕሬዝደንት አፈወርቂ በላኩት መልእከት ውስጥ "ወቅታዊ የጸጥታ ክስተቶች፣ የሶማሊያ ሁኔታ እና በቀይ ባህር ያሉ ሁኔታዎችን" ጨምሮ አንገብጋቢ የሚባሉ ጉዳዮች መነሳታቸውን ገልጿል።
ኢትዮጵያዊ ከራስ ገዟ ሶማሊያ በተፈራረመችዉ የወደብ ስምምነት ምክንያት ከሶማሊያ ጋር ያላት ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ የነበረችው ግብጽ በቅርቡ ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ምድር ማስገባቷ መዘገቡ ይታወሳል።
በዚህ የተቆጣው የኢትዮጵያ መንግስት ሶማሊያ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን ቀጣናውን ለማተራመስ እየሰራች ነው ሲል ከሷል። ኢትዮጵያ ይህን ሁኔታ በዝምታ እንደማታልፈው በውጭ ጉዳይ ሚኒስተሯ በኩል ማስጠንቀቋ ይታወሳል።