ግብጽ ህወሓት እና ኤርትራን ማደራደር እንደምትፈልግ ማስታወቋ ተነገረ
የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን በቅርቡ በሰጡት መግለጫ የትግራይ ክልልና የኤርትራ ባለስልጣናት ንግግር መጀመራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል
የካይሮ ባለስልጣናት ከሰሞኑ በአስመራ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መክረዋል
ግብጽ ህወሓት እና ኤርትራን ማደራደር እንደምትፈልግ ማስታወቋ ተነገረ።
ካይሮ ፍላጎቷን የገለጸችው ባለስልጣናቷ ከሰሞኑ በአስመራ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዘናሽናል ገልጸዋል።
የግብጽ የስለላ ተቋም ሃላፊ ጀነራል ጀማል አባስ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባድር አብደላቲ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባለፈው ቅዳሜ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ላይ በሚደርሱባቸው ጉዳዮች ላይ ንግግር ማድረጋቸው የተነገረ ሲሆን፥ የቀይ ባህር ደህንነትን ማስጠበቅ ላይም መክረዋል ተብሏል።
ከዚህም ባሻገር ለአስርት አመታት ግንኙነታቸው የሻከረውን የኤርትራ መንግስት እና ህወሓት በማቀራረቡ ረገድ ካይሮ ድርሻ እንዲኖራት ጥያቄ ማቅረቧን ነው ምንጮች ለዘናሽናል የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከስድስት አመት በፊት ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ መንግሥት ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማለሳለስ በርካታ እርምጃዎች መውሰዳቸው ይታወቃል።
ይሁን እንጂ ለሁለት ዓመታት ከዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያም ሆነ ከህወሓት ጋር ያላት ግንኙነት ወደቀድሞው እየተመለሰ ይመስላል።
የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ግን የህወሓት እና ኤርትራ መሪዎች ይፋዊ ያልሆነ ዉይይት ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።
ከስድስት ወር በፊት የትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸዉ ረዳ ህወሓትን ወክለዉ በዱባይ በተካሄዱ ዉይይቶች ላይ ተካፍለዉ እንደነበር በማውሳትም ንግግሩ መቀጠሉን መግለጻቸው አይዘነጋም።
አላማችን "የፋኖ ኃይሎችንና የኤርትራን መንግሥት ጨምሮ ከጎረቤቶቻችን ሁሉ ጋር ሰላም መፍጠር" ነዉ ያሉት ዶክተር ደብረፅዮን ከዱባዩ ንግግር በኋላ የተካሄዱት ምክክሮች የትና መቼ እንደተካሄዱ ግን አልጠቀሱም።
የዘናሽናል ዘገባም ግብጽ ስላቀረበችው ህወሓትና የኤርትራ መንግስትን ላደራድር ጥያቄ ከአስመራ ስለተሰጠው ምላሽ ያለው ነገር የለም።
ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን ከቀጠናው ሀገራት ጋር ወታደራዊ ትብብሯን እያጠናከረች ትገኛለች።
ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ኪራይ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረሟ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷ ከሻከረው ሶማሊያ ጋር ባለፈው ወር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማ ወታደሮችና የጦር መሳሪያዎችን ወደ ሞቃዲሾ መላኳ ተሰምቷል። የሶማሊያ ባለስልጣናት ግን ካይሮ ወታደሮቿን ልካለች የሚለውን ዘገባ አጣጥለዋል።
ካይሮ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነቷ ተቀዛቅዟል ወደተባለችው አስመራ በማቅናትም ወታደራዊ ትብብርን ያካተተ “ሁሉን አቀፍ ስምምነት” ለመፈራረም ዝግጅት እያደረገች ነው።
የአብዱልፈታህ አልሲሲ አስተዳደር ከጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ሱዳን ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረሙም ይታወቃል።
የካይሮ ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጋር ወታደራዊ ትብብር መመስረት ዋነኛ ግብ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተጽዕኖ መቀነስና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ላይ ጫናን መፍጠር” ነው ይላሉ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ዲፕሎማት ለዘናሽናል ሲናገሩ።
ግብጽ ግጭትና ጦርነት በማያጣው ቀጠና እጇን ማስረዘሟ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ አቋሟን እንድታለዘብ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ከካይሮ ጋር ባለፈው ወር ወታደራዊ ስምምነት የተፈራረመችው ሶማሊያም ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን ስምምነት ከተገበረች የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ላስታጥቅ እችላለሁ ማለቷ የሚታወስ ነው።