የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ ወደ ኤርትራ አቀኑ
ፕሬዝዳንቱ በቆይታቸው ከኤርትራ እና ሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጋር የሶስትዮሽ ምክክር ያደርጋሉ ተብሏል
ካይሮ፣ ሞቃዲሾ እና አስመራ የሶስትዮሽ ወታደራዊ ጥምረት ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተገልጿል
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ ወደ ኤርትራ አቀኑ።
ፕሬዝዳንት ኤልሲሲ በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግብዣ ነው ወደ አስመራ ያቀኑት።
መሪዎቹ የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት፣ የቀይ ባህር ደህንነት እና ሌሎች የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ተገልጿል።
የግብጽ የደህንነት ኃላፊ አባስ ከማል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ባድር አብደላቲ ባለፈው ወር ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
በወቅቱም ከፕሬዝዳንት አልሲሲ የተላከ ደብዳቤን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ መስጠታቸው አይዘነጋም።
ዛሬ አስመራ የሚገቡት ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ከኤርትራው አቻቸው እና ለሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ትናንት አስመራ ከገቡት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ጋር የሶስትዮሽ ምክክር እንደሚያደርጉ የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ግብጽ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ የሶስትዮሽ ወታደራዊ ጥምረት የመመስረት ትልም እንዳላቸው ያነሱት ዘገባዎች፥ ሀገራቱ በርግጥም ጥምረቱን ከመሰረቱ ቀጠናዊ ውጥረቱ ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት በግብጽ ተደጋጋሚ ይፋዊ ጉብኝቶችን ያደረጉ ሲሆን፥ በየካቲት ወር 2024 ከፕሬዝዳንት ኤልሲሲ ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ በነሃሴ ወርም በኒው አላሜን ከተማ ከፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር በአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባህር ላይ በተደቀኑ አደጋዎች ዙሪያ መነጋጋራቸው አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረመች በኋላ ሶማሊያ ከግብጽ እና ኤርትራ ጋር ወዳጅነቷን ይበልጥ ለማጠናከር እየሞከረች ነው።
ካይሮ በቅርቡ የጦር መሳሪያ እና ወታደሮቿን ወደ ሞቃዲሾ መላኳ መዘገቡን ተከትሎም ኢትዮጵያ ተቃውሞዋን ማሰማቷ ይታወሳል።
ሶማሊያ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን ቀጣናውን ለማተራመስ እየሰራች ነው ሲል የከሰሰው የኢትዮጵያ መንግስት፥ ሁኔታው በዝምታ እንደማያልፈው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኩል ማስጠንቀቁ አይዘነጋም።