የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ መሃሙድ ለሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አስመራ ገቡ
ፕሬዝዳንቱ ከኤርትራው አቻቸው ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸው ከሻከረ ወዲህ ፕሬዝዳት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በተደጋጋሚ ወደ አስመራ አቅንተዋል
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ መሀሙድ ለሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ትናንት አስመራ ገብተዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም በአስመራ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ለሶማሊያው ፕሬዝዳንት እና ልኡካቸው አቀባበል አድርገዋል።
የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂም ኤርትራ የገባው ልኡክ አባል ናቸው ተብሏል።
የሶማሊያ እና ኤርትራ ፕሬዝዳንቶች በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸውን ነው የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ላይ ያጋሩት።
ሀገራቱ ሉአላዊነታቸውን፣ የግዛት አንድነታቸውንና ነጻነታቸውን አስከብሮ ለማስቀጠል ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ሁለቱ መሪዎች ጠንካራና የበለፀገ ሀገር መገንባት የሚቻለው አቅሙ የዳበረ የመከላከያ እና ደህንነት ተቋማት ሲኖር ብቻ መሆኑን ተስማምተዋል።
ኤርትራ የሶማሊያን ብሄራዊ ጦር የምታሰለጥነውም ከዚህ ፖሊሲ በመነሳት መሆኑን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ መናገራቸውን የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር በኤክስ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ጽሁፍ ያሳያል።
መሪዎቹ የአስመራ እና ሞቃዲሾን ሁለንተናዊ የሁለትዮሽ ትብብር በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውም ተገልጿል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በአንድ አመት ውስጥ በኤርትራ መሰል ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሰነድ እንደተፈራረመች ሉአላዊነታችን ተደፍሯል የሚል አስተያየት በመስጠት ተቃውሟቸውን ያሰሙት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን ያደረጉት በኤርትራ እንደነበር ይታወሳል።
በአሁኑ የኤርትራ ጉብኝታቸውም ግብጽ ተሳትፎ እንደምታደርግና የሶስትዮሽ ምክክር ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የሶማሊያው ጋሮዌ ኦንላይን ያስነበበው።
ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ግብጽ የሶስትዮሽ ወታደራዊ ጥምረት ከመሰረቱ የቀጠናውን ውጥረት ሊያባብሰው እንደሚችል ተገልጿል።
ግብጽ ባለፈው ወር የደህንነት ኃላፊዋን አባስ ከማል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ባድር አብደላቲ ከፕሬዝዳንት አልሲሲ የተላከ መልዕክት አስይዛ ወደ አስመራ መላኳ ይታወሳል።
ካይሮ በቅርቡም የጦር መሳሪያ እና ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ምድር መላኳ መዘገቡ አይዘነጋም።
በዚህ የተቆጣው የኢትዮጵያ መንግስት ሶማሊያ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን ቀጣናውን ለማተራመስ እየሰራች ነው ሲል በመክሰስ ይህን ሁኔታ በዝምታ እንደማያልፈው አስጠንቅቆ ነበር።