ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ መደበኛ ስልክ አገልግሎት መቋረጡ ተገለጸ
በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ካሳለፍነው ማክሰኞ ጀምሮ ኤርትራ ወደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው መደወል እንዳልቻሉ ተናግረዋል
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአንድ ወር በፊት ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ማቆሙ ይታወሳል
ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ መደበኛ ስልክ አገልግሎት መቋረጡ ተገለጸ።
በ2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ነበር ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለ20 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት ያደሱት፡፡
ሁለቱ ሀገራት የመደበኛ የስልክ አገልግሎትን ዳግም ካስጀመሩ ከሰባት ዓመታት በኋላ ተቋርጧል፡፡
ይህን ተከትሎም ከሐምሌ 2010 ዓ.ም ጀምሮ መደበኛ የስልክ አገልግሎት ሲሰራ የነበረ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ማለትም ከመስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደተቋረጠ በኢትዮጵያ ከሚኖሩ ኤርትራዊያን ሰምተናል፡፡
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራዊ ለአል-ዐይን እንዳሉት “ከማክሰኞ ከሰዓት ጀምሮ መደበኛ ስልክ መደወል አልቻልኩም” ብለዋል፡፡
በኤርትራ ኢንተርኔት አገልግሎት ባለመኖሩ ምክንያት ቤተሰቦቻችንን የምናገኘው በመደበኛ ስልክ ብቻ ነበር የሚሉት እኝህ አስተያየት ሰጩ አገልግሎቱ መቋረጡ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
“ቀስ በቀስ የኢትዮጵያ እና ኤርትራዊያን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚጎዱ እርምጃዎች እየተወሰዱ መምጣታቸው ያሳዝናል” ያሉን ደግሞ ሌላኛው ኤርትራዊ አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡
መደዋወል እንዳንችል እገዳ የጣለው የትኛው መንግስት እንደሆነ አላወቅንም ያሉት እኝህ አስተያየት ሰጪ በየጊዜው በሚወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት እየተጎዳ ያለው ህዝቡ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በሳምንታዊ የዲፕሎማሲ ስራዎች ዙሪያ መግለጫ በሰጡት ወቅት ስለ ጉዳዩ ለቀረበላቸው ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
አምባሳደር ነቢያት በምላሻቸው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ምንም የተቀየረ ነገር እንደሌላ እና በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የኤርትራ መንግስትም እስካሁን ስለ ጉዳዩ ያወጣው መግለጫ የለም፡፡
በኢትዮጵያ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ተጋላጭ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነሀሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ ማቆሙ ይታወሳል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ እና ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጫለሁ ያለው አየር መንገዱ በኤርትራ ያለው አሰራር አስቸጋሪ እና ከቁጥጥሩ ውጪ መሆኑ ለበረራው መቋረጥ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡