የሱዳን ግጭት ተጨማሪ የክልል ተጫዋቾችን እየሳበ መሆኑም ተነግሯል
የአሜሪካን የሰላም ጥሪዎች ችላ በማለት ግብጽ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን) ለሱዳን ጦር ማቅረቧ ተነግሯል።
ግብጽ የሱዳን ጦር የሚያደርገውን ውጊያ ለማጠናከር ይረዱታል የተባሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለሱዳን ጦር መስጠቷን የጸጥታ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ዎል ስትሪት ጆርናል የደህንነት ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው የመሳሪያ አቅርቦቱ የሱዳንን የእርስ በርስ ግጭት ሊያባብስ የሚችል ነው ብሏል።
በእርምጃው ግጭቱ ይበልጥ አደገኛ ሊሆን የሚችልበት እድል እንዳለ ተጠቁሟል።
ከዚህ ባሻገርም ግጭቱ ተጨማሪ የክልል ተጫዋቾችን እየሳበ መሆኑንም ጋዜጣው ዘግቧል።
የድሮን አቅርቦቱ በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የክልል ኃይሎች ጣልቃ የገቡበት የቅርብ ጊዜ ሁነትም ሆኗል።
ጋዜጣው እንደዘገበው ከሆነ የቱርክ "ባይራክታር ቲቢ 2" ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለሱዳን ጦር ኃይሎች ባለፈው ወር ደርሰዋል።
የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የገቡበት የስልጣን ሽኩቻ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ወደ ግጭት አምርቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሏል።
በዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባ ላይ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ እና የሱዳን ጦር ቃል አቀባዮች አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠየቁም ምላሽ አልሰጡም።