ሩሲያ እና ዩክሬን በሱዳንም እየተዋጉ መሆኑ ተገለጸ
የዩክሬን ልዩ ሀይል ባለፉት 15 ቀናት ውስጥ ብቻ በካርቱም ዙሪያ 14 የድሮን ጥቃት አድርሳለች ተብሏል
ዩክሬን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል በሩሲያ ይደገፋል የሚል እምነት አላት ተብሏል
ሩሲያ እና ዩክሬን በሱዳንም እየተዋጉ መሆኑ ተገለጸ፡፡
አውሮፓ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከባድ ጦርነት እያስተናገደች ሲሆን ሩሲያ እና ዩክሬን የቀጥታ ውጊያ ላይ ናቸው፡፡
ሩሲያ በአፍሪካ ያላትን ፍላጎት ለማሳካት በሚልም ዋግነር በተሰኘው ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን በኩል መሪዎችን እና ተዋጊዎችን እየረዳች እንደሆነ ይገለጻል፡፡
ሞስኮ አውሮፓዊያን በአፍሪካ ላይ ያላቸውን የበላይነት ለመግታት በሚል ዋግነርን እየተጠቀመች ነውም ተብሏል፡፡
በጎረቤት ሀገር ሱዳን የሀገሪቱ ብሔራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይል እርስ በርሳቸው መዋጋት ከጀመሩ ወራትን ያስቆጠሩ ሲሆን በጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው ጦር በዋግነር ይደገፋል ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የዩክሬን ልዩ ሀይል ወደ ሱዳን በመምጣት በሩሲያ ይደገፋል ብሎ በሚያስበው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥም የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ተሸከርካሪዎች፣ ይዞታዎች እና ቡድኑ ይጠቀምባቸዋል ተብለው በተለዩ ኢላማዎች ላይ 14 ጊዜ የድሮን ጥቃት አድርሷል ተብሏል፡፡
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር በሱዳን ስላደረሱት የድሮን ጥቃቶች ምላሽ እንዲሰጥ ተጠይቆም ጥቃቱን አድርሰናል ወይም እኛ አይደለንም ማለት አንፈልግም ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ካርቱምን ዋና ከተማው አድርጎ መንግስት እመሰርታለሁ ሲል ዛተ
በጀነራል ሀምዳን ዳጋሎ የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማግኘት ላይ ነው የተባለ ሲሆን ሞስኮ ለቡድኑ በሶሪያ ካለው ወታደራዊ ማዘዣዋ ወደ ሊቢያ ከዚያም ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ እና ቻድ በኩል በማጓጓዝ ወደ ሱዳን እያስገባች ነውም ተብሏል፡፡
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር ከሩሲያው ዋግነር በሚያገኘው ድጋፍ የአየር ላይ ጥቃቶችን ማምከኛ እና ሌሎች ከባድ የጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም በጀነራል አልቡርሃን በሚመራው የሱዳን ጦር ላይ በካርቱም እና ኦምዱርማን በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠር መቻሉም ተገልጿል፡፡
የሱዳን ብሔራዊ ጦር በበላይነት በተቆጣጠረው ፖርት ሱዳን በትናንትናው ዕለት አዲስ ጦርነት ተጀምሯል የተባለ ሲሆን ስለደረሰው ጉዳት እስካሁን መረጃዎች አልወጡም፡፡
በሱዳን በተከሰተው የእርስር በርስ ውጊያ እስካሁን ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል የተባለ ሲሆን የሟቾች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል፡፡