ግብጽ ከኳታር ጋር ያላትንና ለዓመታት ሻክሮ የቆየውን ግንኙነቷን ለማጠናከር ተስማማች
ከ2017 ወዲህ የሻከረ ግንኙነት ያላቸው ግብጽ እና ኳታር ግንኙነታቸውን ለማሻሻል መስማታቸውና አምባሳደሮችንም መሾማቸው ይታወሳል
ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ዛሬ ከኳታሩ አሚር ታሚም ቢን ሃመድ አል ታኒ ጋር በኢራቅ ባግዳድ ተወያይተዋል
ግብጽ እና ኳታር ያለቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ተስማሙ፡፡
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፋታህ አል ሲሲ እና የኳታሩ አሚር ታሚም ቢን ሃመድ አል ታኒ ዛሬ በኢራቅ ባግዳድ ከተካሄደው ቀጣናዊ የትብብር ጉባዔ ጎን ለጎን በሁለትዮሽ እና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ፡፡
በውይይቱ ፕሬዝዳንት ሲሲ የአረቡን ዓለም አንድነት ሊያጠናክሩ በሚችሉ የልማት መስኮች ላይ ከኳታር ጋር በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ማሳየታቸውን ከጽህፈት ቤታቸው የተገኘው መረጃ አመልክቷል ፡፡
መረጃው የኳታሩ አሚር ሀገራቸው ከግብጽ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለይም ፕሬዝዳንት ሲሲ የአረቡን ዓለም ቀጠና ልማት፣ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውንም ነው ያመለከተው፡፡
አሁን ላይ ተጀመሩት የሀገራቱ ትብብሮችና የተካሄዱ ጉብኝቶች ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች እንደሆኑም አንስተዋል አሚሩ፡፡
ጽህፈት ቤቱ መሪዎቹ የተጀመረውን መልካም ግንኙነት ለማስቀጠል እና ውጤታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት ለመስራት መስማማታቸውንም አስታውቋል፡፡
ግብጽ እና ኳታር ከጎርጎሮሳውያኑ 2017 ጀምሮ የሻከረ ግንኙነት ነው ያላቸው፡፡ ሆኖም ይህን ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ከቅርብ ወራት በፊት ተስማምተዋል፡፡ አምባሳደሮችንም ሾመዋል፡፡
መሪዎቹ በግንባር ሲገናኙም ግንኙነቱ ሻክሮ ከቆየባቸው ካበለፉት 4 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡
ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ዛሬ በተመሳሳይ መልኩ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም ጋር ተገናኝተው የሃገራቱ ግንኙነት መጠናከር በሚችልባቸው መንገዶች ዙሪያ መምከራቸውን አል ዐይን አማርኛ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ስለ ቀጣናዊ ትብብር ይመከርበታል በተባለለት የባግዳዱ ጉባዔ የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ የሳዑዲ፣ የዮርዳኖስ፣ የግብጽ እና የሌሎችም የቀጣናው ሃገራት እና ተቋማት መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡